ገበያው የሚፈልገውን ባለሞያ ማግኘት እየተቸገረ ነው።
ኢንዱስትሪዎቹ ባላቸው ፍላጎትና የትምህርት ተቋማቱ በሚሰጡት የስልጠና አይነት መካከል አለመጣጣም እየታየ ነው።
የትምህርት ስርዓቱ እንደ አዲስ መፈተሸ ከኢንዱስትሪዎች ፍላጎት ጋር እንዲስማማ ሆኖ ዳግም መሰናዳት የግድ የሚለው ጊዜ ላይ ተደርሷል።
የቴክኒክና ሞያ ስልጠና ተቋማትን የትምህርት ስርዓት በተመለከተ በተደረገ ውይይት ላይ ነው ይህ ሀሳብ የተነሳው፡፡
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትን በወጉ ለመምራትና ከጊዜው ጋር እንዲስማማ ሀሳብ በማዋጣት፣ መንገዱንም በመጠቆም ያግዛል የተባለ የቲንክ ታንክ(አሰላሳዮች ቡድን) ዛሬ ይፋ ተደርጓል፡፡
ቡድኑ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ዘለግ ያለ ልምድና እውቀት ያላቸው የሀገር ውስጥና ከውጪ የመጡ ምሁራንና ባለሙያዎች ስብስብ ነው ተብሏል፡፡
ዛሬ በተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን በተሰናዳ ዝግጅት ላይ ሲነገር እንደሰማው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓቱ ጊዜውን እና የገበያውን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ለማስቻል ዳግም ስርዓቱን መፈተሽ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያ ካሚል ዘርፉ ብዙ ለውጥን የሚፈልግ፣ ከግሉ ዘርፍ ጋር መተሳሰር ያለበት፣ ከወቅቱ የገበያ ፍላጎት ጋር የተስማማ መሆን ግድ እንደሚለው አንስተዋል፡፡
ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስርዓቱ ባልተቋረጠ ጥናትና ምርምር መመራት እንዲችል፣ ሁሉም በገባው መልኩ የሚጎትተው እንዳይሆን የሚያግዘው የባለሙያዎች ስብስብ ያስፈልገዋል ተብሏል።
ዛሬ የተመሰረተው የቲንክ ታንክ ወይም የአሰላሳዮች ቡድን ስራም ይኸው ነው ብለዋል፡፡
ዘርፉን ለመቀየር በትምህርት ስርዓቱና ሰልጣኞቹን በሚቀበሉት ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የአስተሳሰብ፣ የባህልና የባህሪ ለውጥ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲው ከቅርብ አመታት ወዲህ በርካታ ማሻሻያ እንደተደረገበት ያነሱት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቡሩክ ከድር ደረጃው እንደ አዲስ ከደረጃ 1 እስከ 8 ሆኖ መዘጋጀቱን አንዱ ለውጥ ነው ብለዋል።
በአዲሱ የደረጃ ለውጥ ሌቭል 6 ወይንም ደረጃ 6 ከመጀመሪያ ዲግሪ አቻ ፣ደረጃ 7 ከ2ኛ ዲግሪ አቻ እንዲሁም ደረጃ 8 ከዶክትሬት ዲግሪ አቻ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
የትምህርት አሰጣጡም 70 በመቶ የተግባርና 30 በመቶ የንድፈ ሀሳብ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ በአዲሱ ፖሊሲ የዲጂታል እውቀት፣ክህሎትና የኮሚኒኬሽን ብቃት ከፍ ያለ ቦታ እንዲኖረው የማድረግ ስራ መጀመሩንም አንስተዋል፡፡
ዛሬ ይፋ የተደረገው የምሀራን እና የባለሙያዎች ስብስብ የሆነው የአሰላሳዮች ቡድን በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ልምድ መነሻ በማድረግ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ይደግፋል ተብሏል፡፡
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments