ለኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩልነትና አንድነት መታገላቸው የሚታወቅላቸው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሀገራቸውን ኢትዮጵያን በተለያዩ መስኮች ያገለገሉ ምሁር ነበሩ፡፡
ሞያዊ አበርክቷቸው ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች ደርሷል፡፡
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፣ በ #ገንዘብ_ሚኒስቴር ከበጀት መምሪያ ዳይሬክተርነት እስከ ገንዘብ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
በገንዘብ ሚኒስትር በሚያገለግሉበት ወቅት፣ በጊዜው በተሟላ የተማረ የሰው ሀይል ያልተጠናከረውን መስሪያ ቤት፣ መልክ ለማስያዝ ከፍተኛ ተግባር መፈፀማቸው ተነግሮላቸዋል፡፡
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የተወለዱት እርሳቸው ከከተማ የራቀች ገጠር በሚሏት ቦርጂ አካባቢ ነው፡፡
አባታቸው አቶ ደመቅሳ ሰንበቶ በልጅታነቸው ቢሞቱም እናታቸው ወይዘሮ ኔሴሴ ሰርዳ እና አጎታቸው አቶ ጎቡ ሰንበቶ ምንም ሳይጎድላባቸው እንዳሳደጓቸውና የዘመናዊ ትምህርት እንዲከታተሉ እንዳደረጉላቸው ያስታወሱ ነበር፡፡
በአስራ አንድ ዓመታቸው በጊምቢ አንደኛ ደረጃ የጀመሩትን ትምህርታቸውን በኩዩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቀጥለው በቀድሞ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ተምረው በ #ኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ድግሪያቸው በከፍተኛ ማዕረግ ለማግኘት ችለዋል፡፡
በአሜሪካው ሲራክዩዝ ዩኒቨርሲቲም በኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ድግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
በሀገራቸው የገንዘብ ሚኒስትርነት ካገለገሉ በኋላ በ #UNDP እና በአለም ባንክ ተቀጥረው አገልግሎታቸውን አለም አቀፍ አድርገውታል፡፡
አቶ ቡልቻ፣ በ17 ዓመታቸው ከመሰረቱት የመጀመሪያ ጋብቻቸው አምስት፣ ከሁለተኛ ጋብቻውም የአንድ ልጅ አባት ናቸው፡፡
የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ፣ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን አጠናክረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲጠናከር ሕዝቦች በእኩልነትና በአንድነት እንዲኖሩ ያላቸውን አቋም በይፋ ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡
በተለያዩ መድረኮች ፖለቲካዊ እምነታቸውን አካፍለዋል፡፡
የፓርላማ አባል ከሆኑ በኋላ፣ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሞያዊ እርምት የሚሰጥ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የአዋሽ ባንክን ከመሰረቱት የጀመሪያዎቹ መስራቾች በመሆን የቢዝነስ ተሳትፎአቸውን ያሳዩ ናቸው፡፡
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የሽምግልና ጊዜያቸውን ለመገናኛ ብዙሃን በሀገር ጉዳይ ምክርና አስተያየት በመስጠት አሳልፈውታል፡፡
አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ዛሬ በ94 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡
Comments