በአፋር ክልል ገቢረሱ ዞን የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ መከሰቱን ዞኑ ለሸገር ተናገረ፡፡
ዛሬ ማለዳ 3 ሰዓት አካባቢ በዞኑ ዱለሳ ወረዳ ሰጋንቶ ቀበሌ ላይ ነው እሳተ ገሞራው የፈነዳው ተብሏል፡፡
በተጠቀሰው አካባቢ ያሉ ተራራ ላይ አዳዲስ ፍንዳታዎች መኖራቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዶ አሊ ነግረውናል፡፡
በፍንዳታው ከሚወጣ ጭስ ጋር አብሮ ጭቃ እየተትጎለጎለ ወደ ላይ ይፈናጠራል ያሉት አቶ አብዶ ጭቃው ሰውነት ላይ ካረፈ በጣም ያቃጥላል ይላሉ፡፡
ከሌሊቱ 9 ሰዓት ጀምሮ ዶፈን ተራራ ላይ የተለያዩ የእሳተ ጎመራ ፍንዳታዎች እንደተከሰቱ የተናገሩት የዞኑ አስተዳደሪ እሳቸው የሰሙት ግን ከማለዳው 3 ሰዓት ላይ የተከሰውን እንደሆነ ነግረውናል፡፡
በአካባቢው ምን እየተካሄደ ነው? ሁኔታው ወዴትስ ያመራል? የሚለውን በተመለከተ የጠየቅነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም ስለፈነዳው እሳተ ገሞራ ለጊዜው መረጃ የለኝም ብሏል፡፡

የፀጥታ ችግሮች እና በመሬት መንቀጥቀጥ በመመዝገቢያ ጣቢያዎቸ ላይ የሚፈፀም ስርቆት በተፈለገው መጠን ሁኔታውን ለመከታተል እንቅፋት ሆኖብኛል ሲል ነግሮናል፡፡
በተጠቀሰው አካባቢ አቅራቢያ ከአዋሽ ፈንታሌ የሚነሳ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ በተደጋጋሚ እየተሰማ መሆኑ ይታወቃል፡፡
እስካሁን ከፍተኛ የተባለው በሬክተር ስኬል መለኪያ 5.1 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ወንድሙ ሀይሉ
Comments