top of page

ታህሳስ 24፣2017 - በአዲስ አበባ በህገ-ወጥ መንገድ ሊሸጥ የነበረ ከ26,000 ሊትር በላይ ነዳጅ ተወረሰ

  • sheger1021fm
  • Jan 2
  • 1 min read

በአዲስ አበባ በህገ-ወጥ መንገድ ሊሸጥ የነበረ ከ26,000 ሊትር በላይ ነዳጅ ተወረሰ፡፡

ነዳጁን ሲሸጡ የተያዙት ማደያዎችና ግለሰቦች ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፤ የተወረሰው ነዳጅም በህጋዊው ገበያ ተሽጦ ከ2.4 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ መንግስት ካዝና ገብቷል ተብሏል፡፡


ይህ ገቢ የተገኘው በመንፈቅ ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ባሉ የነዳጅ ማደያዎች በህግ ከተፈቀደው ውጪ በጄሪካን እየተቀዳ ከተተመነው ዋጋ በላይና ያለ ኤሌክትሮኒክስ መላ ሲሸጥ መሆኑን ተቆጣጣሪው አካል የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ነግሮናል፡፡


ቢሮው ህገወጥ የነዳጅ ግብይትን ለመቆጣጠር ይረዳኛል፣ የማህበረሰቡንም እንግልት ይቀንሳል ብሎ ከሁለት ወራት በፊት በጀመረው ማደያዎችን በቀን ሁለት ጊዜ የመቆጣጠር ስራ በዚህ ተግባር ውስጥ ተገኝተዋል ያላቸውን 9 ማደያዎች ሲሸጡት የነበረውን ነዳጅ ወርሰን አሽገናቸዋል ብሏል፡፡


የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ከ9ኙ ማደያዎች የተወረሰውንም ይጨምራል ያሉን በቢሮው የህጋዊ ተመን ልክ ቡድን መሪው አቶ ደረጀ በቀለ ናቸው፡፡


የዚሁ የቁጥጥር ስራ አካል ነው የተባለው በየቀኑ በአዲስ አበባ ባሉ የነዳጅ ማደያዎች ምን ያህል ምርት እንዳለ በዝርዝር የማሳወቅ ስራ ነዳጅ እያለ የለም የሚሉ ማደያዎች እንዳይኖሩ አድርጓል፤ የተጠቃሚውን እንግልትም ቀንሶታል ብለዋል ሃላፊው፡፡


አሁን በከተማዋ በቂ የነዳጅ አቅርቦት እንዳለ የነገሩን ሃላፊው በየቀኑ በአማካኝ ከ 2 ሚሊዮን ሊትር እስከ 2.8 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን ይሸጣል፤ ናፍጣ ደግሞ በአማካኝ በየቀኑ ከ2.5 ሚሊዮን እስከ 3ሚሊዮን ሊትር እየተሸጠ ነው ብለዋል፡፡


በአቅራቢያችሁ ያለው ማደያ የትኛው አይነት በምን ያህል መጠን አለው የሚለውን በየቀኑ በንግድ ቢሮ ማህበራዊ ትስስር ገፅ የምንለጥፍ ስለሆነ ከዚያ ላይ ተመልከቱ ብለዋል፡፡


ምንታምር ፀጋው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page