top of page

ታህሳስ 23፣2017 - በአዲስ አበባ የድንገተኛ አደጋ ህክምና ለመታከም ከሚመጡት 36 በመቶ በትራፊክ አደጋ ጉዳት ደርሶባቸው የሚመጡ ናቸው ተባለ

በአዲስ አበባ የድንገተኛ አደጋ ህክምና በሚሰጡ የጤና ተቋማት ለመታከም ከሚመጡት ውስጥ 36 በመቶ በትራፊክ አደጋ ጉዳት ደርሶባቸው የሚመጡ ናቸው ተባለ፡፡


#የትራፊክ_አደጋ ከተከሰተ በኋላ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ለማግኘትም ብዙዎች እንደሚቸገሩ ተነግሯል፡፡


በዚህም ምክንያት የትራፊክ አደጋ ከደረሰ በኋላ በቅራቢያ ወደሚገኙ #የጤና_ተቋማት ሳይሄዱ ጉዳቱ ተባብሶ እንደ ጥቁር አንበሳ ወዳሉና የድንገተኛ ህክምና የሚሰጡ የመንግስት የጤና ተቋማት የሚመጡ ብዙዎች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ተናግሯል፡፡


የመንገድ ደህንነቱን የሚያሻሽሉ ስራዎች ለመከወን ከአደጋ በኋላ ያለውን የህክምና አገልግሎት ለማሻሻል የሚከወኑ መሆኑን የተናገሩት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ ናቸው፡፡


ከተከሰቱ የተለያዩ አደጋዎች ውስጥ 36 በመቶ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጐጂ የሆኑ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ የሚሉት አቶ ክበበው፤ ከዚህ ውስጥ ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል እንደ ሀገር አዲስ አበባ ያለው የመንገድ ትራፊክ አደጋዎች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችም አብዛኛዎቹ በ #ፍጥነት ምክንያት የሚከሰቱ መሆናቸውንና አደጋ አድራሾቹም የጭነት ተሽከርካሪዎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ የሆኑ አውቶቡሶች እና ሚኒባሶች ቀዳሚ መሆናቸውን አቶ ክበበው ይጠቅሳሉ፡፡


አደጋ ከተከሰተ በኋላ ቀልጣፋ የህክምና አገልግሎት ማግኘቱ ሊሰራበት እንደሚገባ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ አደጋ ደርሶባቸው የአንቡላንስ አገልግሎት ያገኙት 23.6 በመቶ ፤ በአንድ ሰዓት ውስጥ ደግሞ ወደ ህክምና ተቋም የደረሱት 27 በመቶ ብቻ መሆናቸውን በ2016 በከተማዋ የተከወነው የመንገድ ደህንነት ሪፖርት ያሳያል፡፡


ይህም በተለይ በድህረ አደጋ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉትን ችግሮች እንደሚያሳይና መሻሻልም የሚጠበቅበት መሆኑ ተነግሯል፡፡


ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….


ምህረት ስዩም

Comments


bottom of page