ታህሳስ 22፣2017 - በአዲስ አበባ ካሉ ህንፃዎች የአደጋ መከላከል መስፈርቶችን ያሟሉት 42ቱ ብቻ ናቸው ተባለ
- sheger1021fm
- Dec 31, 2024
- 1 min read
በአዲስ አበባ ካሉ ከ20,000 በላይ ህንፃዎች የአደጋ መከላከል መስፈርቶችን ያሟሉት 42ቱ ብቻ ናቸው ተባለ፡፡
ይህንን ያለው የከተማዋ #እሳትና_አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ነው፡፡
ኮሚሽኑ መስርቶቹን የማያሟሉ የተቋማትና የግለሰብ ህንፃዎች ላይ በቅርቡ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እጀምራለሁ ብሏል፡፡
ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ይከፈለው ወልደመስቀል እንደነገሩን፤ ከ4ኛ ወለል በላይ የሆነ የትኛውም ህንፃ የአደጋ መከላከል መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለበት የሚደነግግ ደምብ ወጥቷል፡፡
ለመሆኑ የአደጋ መከላከል መስፈርቶቹ ምን ምን ናቸው?
አንድ ህንፃ ጅምር የእሳት ማጥፊያ፣ አውቶማቲክ የእሳት አደጋ #መከላከያ ማስገጠም፣ የአደጋ መከላከል ምልክቶችን በሚታይ ቦታ ማስቀመጥ፣ አመቺ የአደጋ ጊዜ መውጫ የግድ ሊኖረው ይገባል ተብሏል፡፡
በተለይ እንደ ሆቴል ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሆኑ የሰለጠኑ የአደጋ ጊዜ ባለሙያዎች ሊኖራቸው እንደሚገባ ተደንግጓል፤ባለሙያዎቹን እኛ እናሰለጥንላቸዋለን ብለውናል፡፡
እነዚህን የተጠቀመጡ መስፈርቶችን አሟልታችሁ ከኮሚሽኑ የማረጋገጫ ደብዳቤ ውሰዱ ያልናቸው ተቋማት ቢኖሩም ለመውሰድ ቸልተኛ ሆነዋል፤ ከዚህ በኋላ በቴልቪዥን ማስታወቂያ ካስነገርን በኋላ ወደ እርምጃ ነው የምንገባው ብለዋል፡፡
በአንድ በኩል በከተማዋ በመገንባት ላይ ያሉት #ህንፃዎች የተቀመጡ አስገዳጅ የደህንነት መስፈርቶችን አሟልተው መሆን አለመሆኑን እናረጋግጣለን በማለት ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከዚህ በኋላ የሚገነባ የትኛውም ህንፃ አስገዳጅ የደህንነት መስፈርቶችን ሳያሟላ ለገንቢው የግንባታ ፍቃድ አይሰጥም ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከ4 ፎቅ በላይ ህንፃ ያላችሁ ግለሰቦችና ተቋማት ሳረፍድ የደህንነት መስፈርቶችን አሟልታችሁ ማረጋገጫ ውሰዱ፤ ይህ ካልሆነ ግን ከገንዘብ ቅጣት እስከ ንግድና የስራ ፍቃድ እስከ መንጠቅ የደረሰ እርምጃ እንደሚወሰድባችሁ እወቁት ብሏችኋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…..
ምንታምር ጸጋው
Comments