ዘምዘም ባንከ በ2016 በጀት ዓመት ከግብር በፊት 148 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ተናገረ።
በበጀት ዓመቱ የባንኩ አጠቃላይ ገቢ 850 ሚሊዮን በላይ መድረሱም ተነግሯል።
ዘምዘምባንክ በትናንትናው እለት የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄዷል።
የባንኩ የዳይሬከተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ናስር ዲኖ(ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት ባንኩ በበጀት ዓመቱ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ በተለያዩ የውጤት መመዘኛዎች ጉልህ ስኬቶችን አስመዝግቧል ብለዋል፡፡
ባንኩ በበጀት ዓመቱ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ38 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 6.8 ቢሊዮን ማድረስ ችሏል፣ ጉባኤው እየተካሄደ ባለበት ታህሳስ 20 ቀን 2017 ላይ ደግሞ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ብር 7.7 ቢሊዮን ደርሷል ብለዋል።

የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መሊካ በድሪ በበኩላቸው የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት የተገኘው የደንበኞች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ66 በመቶ ዕድገት በማሳየት ከግማሸ ሚሊዮን በላይ በመድረሱን ጠቅሰዋል።
ከአጠቃላይ የባንኩ የገንዘብ እንቅስቃሴ ውስጥ አብዛኛዉ በዲጂታል የባንከ አገልግሎቶች በኩል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ወ/ሮ መሊካ በድሪ አስረድተዋል።
በዚህም የዲጂታል ባንከ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 150 በመቶ በላይ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
የዘምዘም ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠን 9.3 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተነግሯል።
ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ36 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡
ባንኩ በአሁኑ ወቅት 89 ቅርንጫፎች፣ ከ1500 በላይ ሠራተኞችን አሉኝ ብሏል።
ዘምዘም ባንክ በያዝነዉ በጀት ዓመት አንሳር ዲጂታል ፋይናንሲንግ የተሰኘ ሙሉ በሙሉ ሸሪዓን መሰረት ያደረገ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት ማቅረቡን አስታውሷል።
ንጋቱ ሙሉ
Opmerkingen