ታህሳስ 19፣2017 - የሴት ሰራተኞቹን አቅም ለማሳደግ የሚረዳ መረሃ-ግብር ማስጀመሩን ዳሽን ባንክ ተናገረ
- sheger1021fm
- Dec 28, 2024
- 1 min read
የሴት ሰራተኞቹን አቅም ለማሳደግ እና ሴት አመራሮችን በብዙ ለማፍራት የሚረዳ መረሃ-ግብር ማስጀመሩን ዳሽን ባንክ ተናገረ።
በታላላቅ ሀገራዊና ተቋማዊ ስኬቶች ጀርባ የሴቶች ሚና ከፍ ያለ ነው የሚሉት የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ሴቶች ተገቢው ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
ከምስረታው ጀምሮ ሴቶችን በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ በመሾም ወደፊት የማምጣት ስራ ሲሰራ መቆየቱ የተናገረው ዳሽን ባንክ ዛሬ ያስጀመረው መርሃ-ግብርም ይሄንኑ ስራ ደጋፊ ይሆንልኛል ብሏል።
ዳሽን ባንክ ዛሬ ያስጀመረው የሴት ሰራተኞቹን አቅም ከፍ ለማድረግ እና ሴት አመራሮችን በብዙ ለማፍራት ይረዳኛል ያለው መረሃ-ግብር ሶስት አላማዎች መያዙ ተነግሮለታል።
“ለባንኩ የወደፊት ከፍተኛ አመራር መሆን የሚችሉ ሴቶችን አስቀድሞ መለየትና ብቁ ማድረግ የመጀመሪያው የፕሮግራሙ አላማ እንደሆነ’’ የተናገሩት የባንኩ የሰው ሐብት ዋና መኮንን ወ/ሮ ህይወቴ ከፈለኝ ናቸው።
የተሻለ ልምድ ያላቸውን ድጋፍ ከሚሹ ሴት ሰራተኞች ጋር በማገናኘት የሙያ ልምድ እንዲለዋወጡ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ደግሞ ሌላኛው ፕሮግራሙ ሊሰራቸው ካቀዳቸው መካከል እንደሆነም ወ/ሮ ህይወቴ አስረድተዋል።
በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚሰሩ የባንኩ ሴት ሰራተኞች እርስ በርስ እንዲደጋፉ እና ሀሳብ እንዲለዋወጡ ማድረግም በመረሃ-ግብሩ የተካተተ ተግባር መሆኑን ሰምተናል።
ንጋቱ ሙሉ
Comments