top of page

ታህሳስ 18፣2017 - የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ማሻሻያ ተደረገለት

  • sheger1021fm
  • Dec 27, 2024
  • 2 min read

በአዲስ አበባ በየዓመቱ የብዙዎችን ህይወት የሚቀጥፈውን የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ በስራ ላይ የነበረው የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ማሻሻያ ተደረገለት፡፡


ስትራቴጂው ከ2010 ጀምሮ ሲተገበር የቆየ ሲሆን ከከተማዋ ጋር የሚራመድና ለውጦችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዳግም መሻሻሉ ተነግሯል፡፡


ከ2017 እስከ 2030 ድረስ ለዓምስት ዓመታት የሚተገበረው #የመንገድ_ደህንነት_ስትራቴጂ በመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ የሚደርስ ሞትና የአካል ጉዳትን በ25 በመቶ ለመቀነስ ያለመ ነው ተብሏል፡፡


የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂውን ይፋ ያደረገው የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ስትራቴጂው የከተማዋ የትራፊክ ፍሰት እንዲሁም የአደጋ መከላከል ስራዎች በሰባት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ብሏል፡፡


የመንገድ ትራፊክ ደህንነት አስተዳደር ሥርዓትን መዘርጋት፣ የተሽከርካሪ ግጭት በሚበዛባቸው ዋና ዋና መንገዶችን ላይ ማተኮር፣ የመንገድ ትራፊክ ግጭትና ጉዳት መረጃ አስተዳደር፣ የድህረ ምላሽና ሌሎችም የሚተገበሩበት እንደሆነ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ ተናግረዋል፡፡


ከዚህ ቀደም በትግበራ ላይ የነበረው የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ ያስመዘግባቸው ለውጦች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ክበበው በዓመት እስከ 600 ሰዎች ይሞቱበት የነበረው #የትራፊክ_አደጋ ቁጥሩን መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡

አሁንም ግን ወደ 382 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ብቻ ህይወታቸውን እንደሚያጡና ከባድ ጉዳትም ቀላል ጉዳትም አጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ጫና አሁንም በጣም ትልቅ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡


አሁን በከተማዋ የ #ኮሪደር_ልማት ጋር የሚጣጣምና የአደጋ መጠኑን ይበልጥ ለመቀነስ እንዲቻል እንዲሁም የከተማዋን ለውጥ የሚመጥን እንዲሆን ተደርጎ ማሻሻያው መደረጉን ተናግረዋል፡፡


የአዲስ አበባን የመንገድ ደህንነት እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሻሻል በከተማው ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የሞተር አልባ ትራንስፖርትን ማስፋፋትና የብዙኃ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ መስራት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ናቸው፡፡


በከተማ አስተዳደሩ ከሚከወኑ ስራዎች ውስጥም የትራንስፖርት ሥርዓቱን ማሻሻል ፣ የመንገድ ግንባታ፣ ለትራንስፖርት የሚውሉ አውቶብሶች ግዥ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ በየመቱ እንደሚመደበለትም አቶ ያብባል ተናግረዋል፡፡


በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሚመራው የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት በ2009 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን የ13 ዓመት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱ ተነግሯል፡፡


የተሻሻለው ስትራቴጂ ለአምስት ዓመታት ስራ ላይ የሚውል ነው ተብሏል፡፡


በትራፊክ አደጋ በሰዎች ሕይወት ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ከፍተኛ የንብረት ውድመት በማስከተል የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚጎዳ በመሆኑም በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተነግሯል፡፡


ምህረት ስዩም


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page