top of page

ታህሳስ 18፣2017 - የመብት ተሟጋች በ ድርጅቶች ላይ እየተጣለ ያለው እገዳ የሲቪክ ምህዳሩን እንዳያጠበው ስጋት ፈጥሯል ተባለ

  • sheger1021fm
  • Dec 27, 2024
  • 1 min read

የመብት ተሟጋች በሆኑ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ እየተጣለ ያለው እገዳ የሲቪክ ምህዳሩን እንዳያጠበው ስጋት ፈጥሯል ተባለ፡፡


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተደጋጋሚ በመብት ተሟጋች የሲቪክ ማህበራት ላይ እየተጣለ ያለው እገዳ በመደራጀት መብት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡


ኮሚሽኑ #የሲቪል_ማህበረሰብ_ድርጅቶች ባለስልጣን በህዳር ወር በተለያዩ 3 ድርጅቶች ላይ እገዳ ማስተላለፉን አቤቱታዎች ደርሰውኛል ብሏል፡፡


የሲቪል ድርጅቶች ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መስራት ሲገባው ከአላማው ውጭ በመንቀሳቀስ የሃገርን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርቷል በሚል የእገዳ ደብዳቤ እንደደረሳቸው አረጋግጫለሁ ብሏል ኢሰመኮ፡፡


እንዲሁም ባለፈው ታህሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ተጨማሪ ሁለት በ #ሰብአዊ_መብት ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈፅመውታል የተባለው ከባድ የህግ ጥሰቶች በዝርዝር ባላስቀመጠ ደብዳቤ መታገዳቸውም አሳሳቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብሏል ኢሰመኮ፡፡

የመብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል፣ የህግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ የተባሉ 3 በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት መታገዳቸው ይታወሳል፡፡


ታህሳስ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ተቆጣጣሪ መ/ቤቱ በፃፈው ደብዳቤ እግዱን አንስቶ የነበረ ቢሆንም በ3 ቀን ውስጥ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ #የእግድ_ደብዳቤ ደርሷቸዋል ተብሏል፡፡


እንዲሁም የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ታህሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ ሌላ 2 ተቋማትን ማገዱን ኢሰመኮ ባደረግሁት ክትትል አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡


በተጠቀሰው ቀን የታገዱትም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ናቸው፡፡


እንዲህ ያለው እገዳ የሲቪክ ምህዳሩን ከማጥበብ ባሻገር በማህበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል ሲልም ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡


በመሆኑም ተቆጣጣሪ መ/ቤቱ የድርጅቶችን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ወደ ስራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ጥሪ አቅርቧል፡፡


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 Website: https://shorturl.at/yCz7q


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page