top of page

ታህሳስ 17፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

የቱርኩ ፕሬዘዳንት ሬቺፕ ታይፕ ኤርዶአን በሶሪያ የሚገኙ ኩርድ አማጺያን ትጥቅ እንዲፈቱ በብርቱ አስጠነቀቁ፡፡

 

ኤርዶአን የኩርድ አማፂያን ትጥቅ ካልፈቱ እንቀብራቸዋለን ሲሉ መዛታቸውን ሬውተርስ ፅፏል፡፡

 

የቱርክ መንግስት በሶሪያ የሚገኘውን የYPG የኩርድ አማፂያን በአገሩ ህገ - ወጥ እና አሸባሪ ሲል የፈረጀው የPKK ተቀጥላ እና አንድ አካል አድርጎ ይቆጥረዋል፡፡

 

የYPG አማጺያን የአሜሪካ የፀረ ሽብር ጦርነት ተባባሪዎች ተደርገው ሲታዩ ቆይተዋል፡፡

 

ቱርክ ግን በኩርድ ታጣቂዎቹ ጉዳይ እንቅልፍ እንደሌላት ይነገራል፡፡

 

በሶሪያ የቀድሞውን ፕሬዘዳንት ባሻር አል አሳድን መንግስት ካስወገደው የታጣቂዎች ጥምረት ውስጥ የቱርክ ወዳጆችም እንዳሉበት መረጃው አስታውሷል፡፡

 

የሩሲያ ጦር ትናንት በዩክሬይን የኤሌክትሪክ አውታሮች ላይ ያነጣጠረ መጠነ ሰፊ ድብደባ ፈፀመች ተባለ፡፡

 

በአመቱም 13ኛው ታላቅ ድብደባ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

የዩክሬይን ጦር ሩሲያ ለድብደባ ከሰደደቻቸው ድሮኖች እና ሚሳየሎች 180ውን አምክኛቸዋለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡

የሩሲያ የጦር ሹሞች ግን በትናንቱ ድብደባ አላማችንን አሳክተናል ብለዋል፡፡

 

የዩክሬይን በምዕራባዊያ ወግ ገናን በትናንትናው እለት ስታከብር 2ኛዋ እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡

 

የዩክሬይኑ ጦርነት ያለ አንዳች የመቆሚያ ምልክት ወደ 3ኛ አመቱ እየተቃረበ ነው፡፡

 

 

በጋዛ ሰርጥ የተኩስ አቁም ላለመደረሱ እስራኤል እና ሐማስ እየተወነጃጀሉ ነው፡፡

 

ተፋላሚዎቹ በካታር እና ግብፅ አመቻችነት ሲደራደሩ መሰንበታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል፡፡

 

እንደውም ወደ ስምምነት ተቃርበዋል ሲባልም ነበር፡፡

 

አሁን ስምምነት ላለመደረሱ እየተካሰሱ ነው ተብሏል፡፡

 

ሐማስ እስራኤል ስምምነት እንዳይደረስ አዳዲስ ቅድመ ሁኔታዎችን እየደነቀረች ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡

 

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትረ ቤኒያሚን ኔታንያሁ ስምምነት እንዳይደረስ ነገሩን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ያደረገው ሐማስ ነው ሲሉ ከስሰዋል፡፡

 

የተኩስ አቁሙ በሐማስ እጅ የሚገኙ ታጋቾችን መለቀቅ እና በምላሹ በእስራኤል የታሰሩ ፍልስጤማውያን መፈታትንም የተመለከተ ነው ተብሏል፡፡

 

 

በእግድ ላይ የሚገኙት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዘዳንት ዩን ሱክ የዎል ከምዝበራ ተከላካይ ሹሞች ዘንድ እንዲቀርቡ ጥሪ ቢደረግላቸውም ሳይገኙ ቀሩ ተባለ፡፡

 

ዩን ሱክ የዎል ከአንዴም ሁለቴ ከመርማሪዎች ዘንድ ሳይቀርቡ መቅረታቸውን ሬውተርስ ፅፏል፡፡

 

ፕሬዘዳንቱ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ ወታደራዊ አስተዳደር ስር እንድትውል ያልተሳካ ሙከራ ማድረጋቸው ጣጣ አምጥቶባቸዋል፡፡

 

የአገሪቱ ፓርላማ ዩን ሱክ የዎል ከሀላፊነት ወርደው እንዲከሰሱ ድምፅ ከሰጠባቸው ሰንብቷል፡፡

 

አሁን ከሀላፊነት ታግደው ይገኛሉ፡፡

 

በምዝበራ ተከላካይ ሹሞች እና በአቃቢያነ ህግ ፊት እንዲቀርቡ በተደረገላቸው ጥሪ ያለመገኘታቸው ለሌላ ጣጣ እየጋበዘባቸው ነው፡፡

 

ተቃዋሚዎች ታስረው ይቅረቡ የሚል ጥሪ ማበርታታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g

 

 

Comments


bottom of page