ታህሳስ 14፣2017 - የድጎማ ምርቶችን ቤት ለቤት በማድረስ ላይ ያለው ''ማኪባ ጠቅላላ ንግድ'' ከዚህም በተጨማሪ ያሻችሁን ባላችሁበት አዝዛችሁ የምትገዙበትን አማራጭ ይዤ እየመጣሁ ነው ብሏል፡፡
- sheger1021fm
- Dec 23, 2024
- 1 min read
በአዲስ አበባ ባሉ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በመንግስት የሚቀርቡለትን የድጎማ ምርቶች ተረክቦ ቤት ለቤት በማድረስ 300ሺህ ሰዎችን እያገለገልኩ ነው የሚለው ማኪባ ጠቅላላ ንግድ አሁን ደግሞ ከዚህ ስራው ጎን ለጎን በግሉ አገልግል ፕላስ በሚል ስያሜ ሁሉንም አይነት ሸቀጦች በመያዝ የቤት ለቤት ግብይት ሊጀምር መሆኑን ነግሮናል፡፡
በበይነ መረብ የሚከወን የኦላይን ንግድ በተበጣጠሰ መንገድ እንደሚሰራ የሚናገሩት የማኪባ ጠቅላላ ንግድ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አዋሽ መሃመድ ፍላጎቱን ታሳቢ አድርገን አገልግል ፕላስ የሚል መተግበሪያ አዘጋጅተናል፣ ከወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ደምበኞች የፈለጉትን ዓይነት እቃ በቴሌብር በመጠቀም ቢያዙን ባሉበት እናቀርባለን ብለውናል፡፡
ከሽንኩርትና ጤፍ ጀምሮ ሁሉንም የግብርና ምርቶች፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችና ሌላውንም በቀጥታ ከአምራቾች ተረክበን ስለምናቀርብ ከእቃው ዋጋ ውጭ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ዋጋ አንጠይቅም የሚሉት አቶ አዋሽ ይህንን ቤት ለቤት ንግድ ስንጀምር ዋናው ዓላማችን ለዋጋ ጭማሪ መነሻ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰውንና አሁን ያለውን የለዘመ የአቅርቦት ሰንሰለት ማሳጠር እንደሆነም ነግረውናል፡፡
በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ቤቶችና ቦታዎች ያሉበትን ትክክለኛ ቦታ የሚያሳይ ካርታ ባለመኖሩ የኦላይን ንግድን አስቸጋሪ አድርጎታል፤ይሁንና ማኪባ ወደ ቤት ለቤት ንግዱ መግባት ሲያስብ አስቀድሞ የደምበኞቹን አድራሻ በኦላይን ሲመዝገብ መቆየቱን ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል፡፡
ድርጅቱ ካዘጋጀው አገልግል ፕላስ ከተባለው መተግበሪያ ባሻገር መተግበሪያውን መጠቀም ለማይችሉ የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ስልክ በመደወል ብቻ የፈለጉትን እቃ ማዘዝ እንዲችሉ የስልክ መስመር እንደሚኖርም አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቋቋመው የአዲስ አበባ ንግድ ስራዎች ድርጅት ምርቶችን የሚያቀርብልን በመሆኑ የአቅራቢ ችግር አይኖርብንም ሲሉ የማኪባ ጠቅላላ ንግድ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አዋሽ መሃመድ ነግረውናል፡፡
ምንታምር ፀጋው

Comments