ታህሳስ 14፣2017 - የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በቅርቡ ይፋ ያደረገው ዝቅተኛ የደሞዝ ጣሪያ አምራቾች አካባቢ አነጋጋሪ እየሆነ መምጣቱን ሰምተናል
- sheger1021fm
- Dec 23, 2024
- 1 min read
በጋርመንትና መሰል ስራ የሚሰማራ ባለሙያ በደሞዝ ክፍያ ብቻ ቀጥሮ ማሰራት አዋጭ አይደለም የሚሉት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች እስካሁን እየተደረገ የነበረው ከደሞዝ በተጨማሪ ሰራተኛው በሰራው ስራ ልክ ከደሞዙ በተጨማሪ ክፍያ እንዲያገኝ እናደርግ ነበር ብለዋል፡፡
ይህ አሰራር ለባለሃብቱም ለሰራተኛውም ጠቃሚ ነው የሚሉት ባለሃብቱ አሁን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የጀመረው አሰራር ግን ጉዳቱ ለአምራቾች ከፍ ያለ ነው ሲሉ ነግረውናል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ከተማ አስተዳደሩ ያወጣው ዝቅተኛ የደሞዝ ጣሪያ አካሄዱህጋዊነት ጥያቄ ቢኖርበትም ዝቅተኛ ደሞዝ ጣሪያ መወሰን ግን አለበት በዚህ ላይ እስማማለሁ ብሏል፡፡
ይህ ችግር እስከወዲያኛው የሚፈታው ወጥ በሆነ መንገድ እንደ ሀገር ዝቅተኛ የደሞዝ ጣሪያ ይፋ ሲደረግ ነው ብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በበኩሉ በማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ባወጣው መረጃ ዝቅተኛ የደመወዝ ጣርያ አስቀመጠ በሚል የሚሰራጭብኝ ዘገባ የተሳሳተ ነው ሲል መግለጫ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን በዚሁ ዘገባው ማጠቃልያ ላይ ደግሞ ዝቅተኛ ደሞዝ ጣሪያ ለግብር ከፋዮች አስቀምጦ እያስከፈለ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
በረከት አካሉ

Comments