በተለይም በሀገር ውስጥ በረራ በአየር ማረፊያዎች አይነስውራን ለአቅጣጫ መጠቆሚያ የሚይዙትን ዘንግ እና የእግር ጉዳት ያለባቸው የሚጠቀሙበትን ክራንች ይዘው ወደ አውሮፕላን መግባት አይችሉም ተብሏል፡፡
የተጠቀሱት #አካል_ጉዳተኞች የሚጠቀሙባቸው ቁሶች አውሮፕላን ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክልን በካርጎ እንዲጫኑ የሚደረግ መሆኑ የአየር ትራንስፖርትን ለአካል ጉዳተኞች አስቸጋሪ እንዳደረገው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተናግሯል፡፡
ኮሚሽኑ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች ያለው የተደራሽነት ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
አደረኩት ባለው ክትትል አየር ማረፊያዎች ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ ተሽከርካሪ ወንበሮችና ረዳት በበቂ ሁኔታ እንደሌላቸው ታዝቢያለሁ ብሏል፡፡
ዊልቸር እና የአካል ድጋፍ ለሚጠቀሙ አካል ጉዳተኞች የተዘጋጀ ምቹ የግል መፈተሻ ክፍል እንደሌለም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ወደ አውሮፕላን ለመግባትም ሆነ ከአውፕላን ለመውረድ የመጓጓዣ አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች ስለማይሰጥ ለተጨማሪ እንግልት እየተዳረጉ ነው ተብሏል፡፡
በተለይም የአውሮፕላን በሮች ላይ የሚገጠም ተሻጋሪ ድልድይ እንዲሁም የአውሮፕላን ደረጃዎችን የሚያሻግር መኪና በሀገር ውስጥ በረራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የለም ብሏል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፡፡
በዓይነ ስውራን እና መስማት ለተሳናቸውም በአየር መንገዱ ሲስተናገዱ በቂ መረጃ እንደማይሰጣቸው በሰብአዊ መብት ሁኔታ ምርምራዬ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በ #ኢሰመኮ የሴቶች ፣ የህፃናት የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግብ ገብረሃዋርያ አየር መንገዱ አካል ጉዳተኞችን በአገልግሎቱ አካታች ለማድረግ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ በተሰጠው ምክረ ሀሳብ መሰረት የተወሰኑ ማስተካከያዎችን ማድጉን አድንቀዋል፡፡
እንደማሳያ የአካል ጉዳተኛ መንገደኞች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በበይነ መረብ ትኬት ለመቁረጥ ለአይነ ስውራን ተደራሽ ያልነበረው የሞባይ መተግበሪያ በማሻሻያ ተደራሽ ማድረጉ አንዱ ነው ተብሏል፡፡
አየር መንገዱ የሚሰጠው አገልግሎት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ እንዲሆን የተሰጠውን ምክረ ሀሳብ ለመተግበር የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ለሚወስዳቸው የማስተካያ እርምጃ ዝርዝር እቅድ አዘጋጅቶ ለኢሰመኮ መላኩንም ሰምተናል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Commentaires