top of page

ታህሳስ 10፣2017 - ''አጋቾች በባንክ የሚያደርጉትን የገንዘብ ዝውውር መቆጣጠሪያ በባንኮች ሊኖር ይገባ ነበር ይህ የእኛም ጥያቄ ነው'' የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈፀሙ #የእገታ_ወንጀሎች በአጋቾች የሚጠየቀው የቤዛ ክፍያ በባንክ ተከፈለ ሲባል ይደመጣል፡፡


ታጋቾቹን ለማስለቀቅ በታጋች ቤተሰቦችና በአጋቾቹ መካከል በሚደረግ ድርድር አጋቾቹ በሚመርጡት የገንዘብ መቀበያ መንገድ ገንዘቡ እንደሚላክ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ ታገተብን የሚሉ ሰዎች ወደ መገናኛ ብዙሃን ብቅ ብለው ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡


ለአብነትም ባሳለፍነው ነሐሴ 24 2016 ዓ.ም በ #ጎንደር_ከተማ ከመኖሪያ ቤቷ ታግታ የተወሰደችው የ2 ዓመቷ ህፃን ኖላዊት ዘገየ ጉዳይ ብዙዎችን ያሳዘነ እንደነበር ይታወሳል፡፡


በአጋቾቹ ለቤዛ ክፍያ 1 ሚሊዮን ብር ተጠይቆ የነበረ ቢሆንም በድርድር ገንዘቡ ወደ 300 ሺህ ብር ቀነሰ፣ ኋላም 200 ሺህ ብር ተዋጥቶ ለአጋቾቹ የተሰጠ ቢሆንም ህፃኗን መግደላቸው የዚያን ወቅት አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡


ይህንን ያነሳነው መንግስት ራሱ ስለመፈፀሙ እውቅና የሰጠበት እገታ ጉዳይ መኖሩን ለማንሳት እንጂ ተመሳሳይ ብዙ ታሪኮች የብዙዎችን ቤት እንዳናኳኩ ይነገራል፡፡


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው ሪፖርቶቹ እገታ የገንዘብ ማግኛ መንገድ እየሆነ መምጣቱን ይናገራል፡፡


ለመሆኑ በዚህ መንገድ ለሚፈፀሙ እገታዎች በ #ባንክ የሚደረገውን የገንዘብ ዝውውር በመጠቀም እገታ ፈፃሚዎቹን ለምን መያዝ አልተቻለም ስንል የፌድራል ፖሊስ ኮሚሽንን ጠይቀናል፡፡


አቶ ጄይላን አብዲ በኮሚሽኑ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ ናቸው፡፡


እገታዎቹ በአብዛኛው የሚፈፀሙት አሸባሪ ባሉዋቸው ቡድኖች እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጄይላን እነርሱን በቀላሉ ማግኘት አለመቻሉ አንዱ ችግር ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ ቡድኖች በባንክ የሚያደርጉትን የገንዘብ ዝውውር መቆጣጠሪያ መንገድ በባንኮች ሊኖር ይገባ ነበር ይህ የእኛም ጥያቄ ነው ብለውናል፡፡


በሌላ በኩል እገታዎች እንዲበራከቱ አንዱ ምክንያት የሆነው በማህበራዊ ሚዲያ ስለ እገታ የሚነገርበት መንገድ ነው፤ የሚዘገበው ወንጀሉን ሊስቆምና ሊያስጠነቅቅ በሚችል መልኩ ሳይሆን ጉልበተኛ ሁሉ በእገታ ገንዘብ ሊያገኝ እንደሚችል ጥቆማ በሚመስል ሁኔታ መዘገቡ እንደሆነ ፖሊስ ኮሚሽኑ ባደረገው ዳሰሳ ተመልክቷል ብለዋል አቶ ጄይላን፡፡


እንዲህ ያሉ የእገታ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥቆማ መስጫ የሞባይል መተግበሪያ ( tiny.cc/TiqomaMescha ) አልምቶ ወደ ስራ ማስገባቱንም ነግረውናል፡፡


ፖሊስ ኮሚሽኑ የእገታ ወንጀሎች ሲፈፀሙ ተከታትሎ ለመያዝ እንድችል የሞባይል መተግበሪያ የወንጀል አፈፃፀሙን በዝርዝር ብትነግሩኝ ተከታትዬ መያዝ እችላለሁ ብሏል፡፡


መረጃ ሰጪዎች ማንነታቸውን መግለፅ ካልፈለጉ ሚስጥራቸው ይጠበቅላቸዋል፤ በዚህ መንገድ መረጃዎችን በመቀበል ወንጀል ፈፃሚዎችን ለህግ እያቀረብኩ ነው ብሏል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Comments


bottom of page