top of page

ታህሳስ  10፣2016 - ቢጂአይ -ኢትዮጵያ የተወሰደበትን የገበያ ድረሻ ለማስመለስ ለመጪዎቹ 5 ዓመታት በዓመት እስከ 10 ቢሊዮን ብር ድረስ እንደሚያፈስ ተናገረ

  • sheger1021fm
  • Dec 20, 2023
  • 2 min read

ቢጂአይ -ኢትዮጵያ የተወሰደበትን የገበያ ድረሻ ለማስመለስ ለሚያከናውናቸው ስራዎች ለመጪዎቹ 5 ዓመታት በዓመት ከ7 እሰከ 10 ቢሊዮን ብር ድረስ  መዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈስ ተናገረ።

 

በዚህ የማስፋፊያ እና የማዘመን ስራ ውስጥ ከኩባንያው የሚሰናበቱ እንዲሁም የሚቀላቀሉ ሰራተኞች አሉ ብሏል።

 

ቢጂአይ-ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የሚያደርገው ኢንቨስትመንት በአሁኑ ሰዓት በዓመት የሚያመርተውን 5 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር በእጥፍ በማሳደግ 10 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር እንደሚያደርሰው  ዋና ስራ አስፈጻሚው ሄርቬ ሚልሃድ ተናግረዋል።


ኢንቨስትመንቱ የኩባንያውን ፋብሪካዎች የማምረት አቅም መጨመር እና እንዲሁም ታሪካዊውን የአዲስ አበባ ፋብሪካ ሰበታ እና ማይጨው ወደሚገኙት ሁለቱ የቢራ ፋብሪካዎቹ ማዛወርን ያካትታል ብሏል።

 

በአዲስ አበባ ሜክሲኮ የሚገኘውን የማምረቻ እና ዋና መስሪያ ቤቱን ለፐርፐዝ ብላክ የሸጠው ቢጂአይ ኢትዮጵያ  ይህ ሊሆን የቻለውም በውሃ አቅርቦት ውስንነትና በሎጂስቲከስ ችግሮች ምክንያት ነው ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው አስረድተዋል።

 

ፐርፐዝ ብለክ ለፉብሪካው ግዢ ጥሩ ገንዘብ አቅርቧል ያሉት ሀላፊው መጠኑን ከመጥቀስ ተቆጥበው ክፍያውም በጥሩ አፈፃፀም እየሄደ ነው ብለዋል።

 

የኩባንያው  ዋና መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ውስጥ እንደሚሆን ያስረዱት ስራ አስፈጻሚው ይህም የት እንደሚሆን በመጪዎቹ ስድስት ወራት ይታወቃል ብለዋል።

 

ሌሎቹ የሜክሲኮው ፋብሪካ እቃዎች ወደ ሰበታ እንዲሁም የጠርሙስ ማምረቻው ደግሞ ወደ ራያ ይዘዋወራሉ ብለዋል።

 

ይህም በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ መታቀዱ ተሰምቷል።

 

ቢጂአይ  በኢትዮጵያ ያሉትን ሰባት ፉብሪካዎቹን ለአስተዳደር በሚያመች መልኩ በቢጂአይ ጥላ ስር እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ስራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል።

 

የሚሰሩት ስራ ሳይኖራቸው ዝም ብለው ተመድበው የሚገኙ፣ ስራው የሚፈልገውን የእውቀት ደረጃ የሌላቸው ሰራተኞች በተገቢው መንገድ ተሰናብተው በምትካቸው የኩባንያውን የወደፊት የመለወጥ ወጥን  ከግብ ለማድረስ የሚያግዙ እውቀት እና ክህሎት ያላቸው ሰራተኞች እንደሚቀጠሩ ሲነገር ሰምተናል።

 

ኩባንያው ከጊዜያቸው በፊት ቀድመው ጡረታ የወጡና እድሚያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ የኩባንያው ጉምቱ ሰራተኞች እንዳገለገሉባቸው ዓመታት መጠን እስከ 48 ወራት የሚጠጋ ደሞዝ በመክፈል  ማሰናበቱንም ሀላፊው ጠቅሰዋል።


 ኩባንያው ምርቶቹን የሚያከፋፍሉለትን ከነባሮቹ በተጨማሪ አዳዲስ  ድርጅቶችም እንደሚመርጥ  ተናግሯል ።


ይህ የሚደረገውም የሽያጭ አሰራሩን በማዘመን የሽያጭ ሰራተኞችና ወኪሎች ወደ ደንበኞች የበለጠ ቀርበው እንዲሰሩ ለማስቻል በማሰብ ነው ተብሏል።

 

በየአካባቢው ያለው የፀጥታ መደፍረስ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ አለማግኘት በስራዬ ላይ እንቅፋት ሆነውብኛል ሲል ኩባንያው አስረድቷል።

 

ቢጂአይ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባሉት ሰባት ፋብሪካዎቹ 3,500 ቋሚ  እና 2,000 ጊዜያዊ ሰራተኞች አሉኝ ብሏል።

 

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሜታ አቦ ፋብሪካን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም በማይጨው (ራያ)፣ በኮምቦልቻ፣ በሀዋሳ፣ በዘቢዳር እና በዝዋይ የሚገኙት ፋብሪካዎች አሉት።

 

ኩባንያው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራን፣ ካስቴል ቢራ፣ ሜታ ቢራ፣ እንዲሁም የተለያዩ አይነት የወይን ምርቶችን እና ስንቅ ከአልኮል ነፃ መጠጥ ያመርታል።

 

ቢጂአይ ኢትዮጵያ በዓመት ከ7.4 ቢሊዮን ብር በላይ ታክስ በመክፈል በኢንዱስትሪው የፕላቲኒየም ግብር ከፋይ ነኝ ብሏል።

 

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page