top of page

ታህሣስ 2፣2017 - የወንጀል ተግባራት ዓይነትና አፈፃፀማቸው እየረቀቀ መምጣቱ ሲነገር ይደመጣል

የወንጀል ተግባራት ዓይነትና አፈፃፀማቸው እየረቀቀ መምጣቱ ሲነገር ይደመጣል፡፡


ዓይነትና አሰቃቂነታቸው እየከፋና ከማህበረሰቡ ወግና ባህል ያፈነገጡ፣ ፈፃሚዎቹም የተጠያቂነት ጉዳይ ሳያሳስባቸው በቪዲዮ ጭምር እየቀረፁ ሲፈፀሙ ይታያል፡፡


እንዲህ ዓይነቱ ነገር ለምን ተበራከተ፤ ለዚህ ያደረሰን ገፊ ምክንያት ይኖር ይሆን ስንል በጉዳዩ ዙሪያ የህግ ባለሙያ ጠይቀናል፡፡

አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ የህግ ባለሙያና ጠበቃ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት አሰቃቂና ነውር የተሞላባቸው ወንጀሎች ሲፈፀሙ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ እየተመለከትን ነው፤ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ወደ ህግ ቀርበው የፍርድ ውሳኔ እየተሰጣቸው አለመሆኑ ደግሞ መጪውን ጊዜ እንድንፈራው ያደርጋል ይላሉ፡፡


እነዚህ ሰዎች የተጠያቂነት ጉዳይ የማያሳስባቸው በብሔራቸው፣ ወይም በገንዘባቸው ስለሚከለሉ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡


ከዚህ ቀደም ይፈፀሙ የነበሩ ወንጀሎች ያን ያህል ያልተወሳሰቡና የሚታወቁ ዓይነት እንደነበሩ በስራቸው ምክንያት እንዳስተዋሉ የሚናገሩት የህግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ አሰቃቂ ወንጀሎች በባህሪያቸው የሚበዙት የህግ የበላይነት በማይከበርባቸው በተለይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች እንዳሆነ ጠቅሰዋል፡፡


ስለሆነም ወንጀሎቹ እንዳይፈፀሙ ለማድረግ የህግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ከመንግስት ይጠበቃል ይላሉ፡፡


እንደ ባለሙያው ገለፃ ሌላውና በኢትዮጵያ ወንጀል እንዲበራከት ምክንያት እየሆነ ያለው አንድ ወንጀል ብሰራ ማረሚያ ቤት ገብቼ ተቀልቤ ነው የምወጣው ሌላ የሚመጣብኝ ነገር አይኖርም የሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፡፡


ስለዚህም ለዚህ መፍትሄው ወንጀል ፈፅመው በፍርድ ቤት የእስር ቅጣት የሚወሰንባቸውን ግለሰቦች መንግስት አስቀምጦ መቀለብ የለበትም፤ ታሳሪዎች ቀለባቸውን እራሳቸው እንዲችሉ ቢደረግ ቀለብ አቅራቢ የሌለው ሰው እንደሚራብ ስለሚያውቅ ሌላው ከወንጀል እንዲታቀብ ያደርጋል፤ይህንን ለማድረግ ደግሞ የህግ ማሻሻያ ቢደረግ ባይ ናቸው፡፡


በማረሚያ ቤቶች ያለው የታሳሪዎች ቅበላ፣ አያያዝና ቅበላ ላይ የህግ ማሻሻያ ያስፈልጋል የምለው በአሁኑ ወቅት ማረሚያ ቤቶች በእስረኞች እየተጨናነቁ በመሆኑንና በዓላት በመጡ ቁጥርም በይቅርታ በሚል በትክክል መታረም አለመታረማቸው ሳይረጋገጥ ሲለቀቁ ስለምመለከት ነው፤ ስለዚህም ማሻሻያው በሚመለከታቸው አካላት ይታሰብበት ሲሉም መክረዋል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page