ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በወሊድ ይገኝ የነበረውን የዜግነት መብት አስቀራለሁ አሉ፡፡
አሜሪካ በምድሯ ለሚወለዱ የተለያዩ ሀገር ሰዎች ልጆች የዜግነት መብት ስትሰጥ ቆይታለች፡፡
ተመራጩ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ይህን በወሊድ የሚገኙት የአሜሪካዊነት የዜግነት መብት ዋይት ሐውስ ስገባ በፕሬዘዳንታዊ ትዕዛዝ እሽረዋለሁ ሲሉ ለNBC ነግረውታል፡፡
በልጅነታቸው በስደት አሜሪካ የገቡ ስደተኞችን ለመርዳት ፈቃደኛ መሆናቸውን ፣ ለዚህም ከዴሞክራቶች ጋር አብረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ትራምፕ ነጩ ቤት ሲገቡ ሰነድ አልባ ሰዎች በገፍ ወደየሀገሮቻቸው እንመልሳቸዋለን ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ቤተሰብ አይነጣጥልም ወይ? ተብለው የተጠየቁት ትራምፕ ቤተሰብ መለያየት አያስፈልግም ለዚህ መፍትሄው ደግሞ ሁሉንም በአንድ ላይ ከሀገር ማባረር ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡
ትራምፕ በሚቀጥለው ጥር ወር ሀላፊነታቸውን ይረከባሉ፡፡
እስራኤል በሶሪያ የኬሚካል የጦር መሳሪያ ይገኝባቸዋል ባለቻቸው ይዞታዎች ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት መፈፀሟ ተሰማ፡፡
የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ጥቃት የሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆን ጭምር ያካተተ መሆኑንን ቢቢሲ ዘግቧል።
መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገ የሶሪያ ሰብአዊ መብት ተከታታይ መ/ቤት እንዳለው እስራኤል በሶሪያ ምድር ከ100 በላይ ጥቃቶችን አድርሳለች ብሏል፡፡
የጥቃቱ ኢላማዎችም መካከል ኬሚካል ጦር መሳሪያ ማምረቻ ይገኙበታል ሲል የወሬ ምንጩ አውርቷል፡፡
እስራኤል የባሻር አልአሳድን መንግስት መውደቅን ተከትሎ የኬሚካል የጦር መሳሪያዎች በአክራሪ ታጣቂዎች እጅ እንዳይገቡ አደርጋለሁ ማለቷን ዘገባው አሰታውሷል፡፡
ሶሪያ የት እና ምን ያህል የኬሚካል መሳሪያ ክምችት እንዳላት የሚታወቅ ነገር ባይኖርም የቀድሞው ፕሬዘዳንት በሽር አልአሳድ የተወሰነም ቢሆን ሊኖረው እንደሚችል መገመቱን በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
አሜሪካ በሶርያ በሚገኝ ዳኤሽ ታጣቂዎች ይዞታ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈፅሜያለሁ አለች፡፡
የአሜሪካ ጦር ባወጣው መግለጫ እንዳለው የአየር ላይ ጥቃቱ ዒላማ ያደረገው በማዕከላዊ ሶሪያ ውስጥ የሚገኙ የዳኤሽ ይዞታዎችን ነው፡፡
በዚህም የISIS መሪዎች ፣ ካምፖች መመታቸውን TRT ዎርድ ዘግቧል፡፡
የጥቃቱ አላማም ISIS በሶሪያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተጠቅሞ ወደፊት እንዳይል በማሰብ ነው ተብሏል፡፡
በጥቃቱ ምን ያህል “ሽብርተኛ” ሲል የጠራቸው ታጣቂዎች እንደተገደሉ ያለው ነገር የለም፡፡
በሶሪያ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባሻል አል አሳድ ሀገር ጥለው መኮብለላቸውና አማጺያን ሀገሪቱን ዋና ዋና ከተሞና መ/ቤቶች መቆጣጠራቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
በኒጀር ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 21 ንጹሃን ሰዎች መገደላቸው ተሰማ፡፡
21 ሰዎች ግድያ የተፈፀመባቸው ከገበያ ሲመለሱ ተሳፍረውበት ለነበረ ተሽከርካሪ ላይ በተፈፀመ ጥቃት መሆኑንን አናዶሉ ዘግቧል፡፡
ግድያው የተፈፀመበት ስፍራም ኒጀር ፣ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ በሚዋሰኑበት የድንበር አቅራቢያ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የአገሪቱ ጦሩ ፅንፈኞች ይንቀሳቀሱበታል በተባለው በዚያ አካባቢ ተደጋጋሚ ዘመቻዎች ቢያደርግም ታጣቂዎቹን ከጥቃታቸው ሊያስቆማቸው አልመቻሉን ዘገባው አስታውሷል፡፡
በአካባቢው የታጣቂዎች ጥቃት እንደሚደጋገም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comentários