ማንኛውም ሰው የፕላስቲክ የእቃ መያዣ ቀረጢት ይዞ ከተገኘ ከ5,000 እስከ 10,000 የሚያስቀጣው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡
ረቂቅ አዋጁን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለውሃ መስኖ እና ቆላማ አካባቢ ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መርቶታል፡፡
ይህ በመላው hገሪቱ በ #ደረቅ_ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ተፈፃሚ ይሆናል የተባለው ረቂቅ አዋጅ 6 ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከምንጩ ደረቅ ቆሻሻን መቀነስ መልሶ መጠቀም እና በአግባቡ ማስወገድ መሰረታዊ መርሆቹ ናቸው ተብሏል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የፕላስቲክ ምርት አምራቾች ላይ የሚከተሉትን ሀላፊነቶች ደንግጓል፡፡
በዚህም የ #ፕላስቲክ ምርቱ የአገልግሎት ዘመኑ ሲያበቃ እንዲሰበሰብ ለዳግም ጥቅም ወይንም መልሶ ሁደት ላይ ሊውል የሚችልበትን ሥርዓት መፍጠር የፕላስቲክ ምርቱ የአገልግሎቱ ዘመን እንዳበቃ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስፈልገውን ወጪ የመሸፈን ግዴታ በአምራቹ ላይ ጥሏል፡፡

የደረቅ ቆሻሻን ስለመሰብሰብ በተመለከተም ከሚመለከተው አካል በሚሰጥ ፈቃድ ለጥሬ ምርትነት ካልሆነ በስተቀር ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትም የሚከለክል ነው፡፡
ረቂቅ አዋጁ የደረቅ ቆሻሻን አወጋገድን በተመለከተም ማንኛውም ሰው ለዚህ ዓላማ ተብሎ ከተለየ ቦታ ውጪ ደረቅ ቆሻሻን ማስወገድ እንደማይቻል ጠቁሟል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ልዩ ልዩ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን በተመለከተም ማንኛውም ሰው ከ #መኖሪያ_ቤት ይዞታው ድንበር አንስቶ ቢያንስ እስከ 20 ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማፅዳት ሀላፊነት አለበት፡፡
ማንኛውም አገልግሎት ሰጪ ወይንም የንግድ ተቋም ከይዞታው ድንበር አንስቶ ቢያንስ እስከ 50 ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን የማጽዳት ሀላፊነት አለበት፡፡

ጠርሙስ፣ ጣሳ፣ የታሸገ ውሃ መያዣ ፕላስቲክን በተመለከተም ረቂቁ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የንፅህና መጠበቂያ እና የመዋቢያ ምርቶችን በጠርሙስ፣ በጣሳም ወይም በፕላስቲክ መያዣ የሚያመርቱ፣ የሚያስመጡ፣ የሚያከፋፍሉ ሰዎች ጠርሙስ ወይንም የቆርቆሮ ጣሳ የአገልግሎት ዘመኑ እንዳበቃ መልሶ የሚወገድበትን ዘዴ የመዘርጋት ግዴታ አለበት ይላል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ የላስቲክ የእቃ መያዣዎችን ወደ ሀገር ማስገባት፣ ማምረት፣ መሸጥና ማከፋፈልን ይከለክላል፡፡
ይህን አድርጎ የተገኘም ከ50,000 ብር እስከ 200,000 ብር የገንዘብ ቅጣት እና ከ5 ዓመት ያልበለጠ ፅኑ እስራት ይጠብቀዋል ተብሏል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments