top of page

በፊንቴክ ኢንቨስትመንት ማጭበርበር የተጠረጠሩ አርቲስቶችና ቲክቶከሮች በክስ መቃወሚያቸው ላይ ብይን ተሰጠ::

  • Aug 5
  • 1 min read

ሐምሌ 29 2018


በፊንቴክ ኢንቨስትመንት ማጭበርበር የተጠረጠሩ አርቲስቶችና ቲክቶከሮች በክስ መቃወሚያቸው ላይ ብይን ተሰጠ::


ተከሳሾቹ በማህበራዊ ሚዲያ የሰጡትን መግለጫ በተመለከተም ዐቃቢ ህግ አቤቱታ አቅርቧል።


በ"ፊንቴክ" ኢንቨስትመንት ሽፋን በተፈጸመ መጠነ-ሰፊ የማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ታዋቂ አርቲስቶችና ቲክቶከሮች፣ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ መወሰኑ ይታወሳል።


የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ተከሳሾች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ እና ዐቃቤ ሕግ የሰጠውን መልስ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዛሬ፣ ሐምሌ 29 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።


በዛሬው የችሎት ውሎ፣ ተከሳሾቹ "እኛ የሠራነው የማስታወቂያ ሥራ እንጂ ኮምፒውተር ተጠቅመን የፈጸምነው የማጭበርበር ወንጀል የለም" ሲሉ 1ኛ ተከሳሽ በ5 ገጽ፣ ሌሎች ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው በ6 ገጽ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎታል።


በሌላ በኩል፣ ተከሳሾቹ ሰሞኑን "እግረኛው" በተሰኘ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ቀርበው መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ባለ 5 ገጽ የክስ አቤቱታ ለችሎቱ አቅርቧል።


ዐቃቤ ሕግ በአቤቱታው፦ በፍርድ ቤት በሂደት ላይ ባለ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት በፍትሕ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር፣ ፍርድ ቤቱ ለሁለት ወራት ያህል ከመዘጋቱ በፊት አቤቱታው ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት፤ ወይም ይህ ድርጊት ወንጀል በመሆኑ ፍርድ ቤቶች በተዘጉበት ወቅትም ቢሆን ችሎቱ አስቸኳይ ብሎ በሚያያቸው ጉዳዮች ውስጥ ተካቶ እንዲታይለት ጠይቋል።


የተከሳሾች ጠበቃ በበኩላቸው አቤቱታውን አንብበው ለመረዳት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ፣ እንዲሁም መግለጫ የተሰጠበት ማህበራዊ ሚዲያ ጋዜጠኛ የሆነው ተክለሃይማኖት አዳነ እና በመግለጫው ወቅት የተገኙት ጠበቃ አበባው አበበ በችሎቱ ባለመገኘታቸው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።


ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ፣ የማንኛውም ሰው የመናገርና ሀሳብን የመግለጽ መብት ሕገ-መንግሥታዊ ቢሆንም፣ በሕግ በተያዘ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠትን በተመለከተ ዝርዝሩን ለማጣራት ጋዜጠኛ ተክለሃይማኖት አዳነ እና ጠበቃ አበባው አበበ በችሎት ተገኝተው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ለጥቅምት 02 ቀን 2019 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።


ገዛ ጌታሁን

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page