top of page

በኢትዮጵያ የጭነት ማስተላለፍ ስራ ለውጭ ባለሃብቶች ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆን ተወስኗል።

  • Jul 1
  • 2 min read

ሰኔ 24/2018


በኢትዮጵያ የጭነት ማስተላለፍ ስራ ለውጭ ባለሃብቶች ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆን ተወስኗል።


ከዚህ ቀደም የውጭ ኩባንያዎች ከ49 በመቶ ያልበለጠ ድርሻ ይዘው ከአገር ውስጥ ባለሃብቶች ጋር በጥምረት እንዲሰሩ ነበር የሚፈቀድላቸው።


ገደቡ የሎጂስቲከስ ዘርፉ የሚፈለገው ያህል የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ፤ውሳኔውን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ አመልክቷል።


ዝርዝር የህግ ማዕቀፎችን የማጠናቀቅ ስራ በሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት በኩል እየተከወነ እንደሚገኝም ጠቅሷል።


የኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ አገልግሎት አሰጣጥ ዝቅተኛ እንደሆነ በየጊዜው የሚወጡ የአለም ባነክ ሪፖርቶች ያሳያሉ የሚሉት ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሎጂስቲክስ እና የንግድ ሠንሠለት ማኔጅመንት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ማቲዮስ ኢንሰርሙ የአሁኑ ውሳኔ ይህንን የሚቀይር እንደሚሆን ተናግረዋል።



ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ፤ ከኢትዮ - ጁቡቲ ምድር ባቡር እና ከኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ውጪ ያሉና ፤በሎጅስቲክስ ዘርፉ ላይ የተሰማሩት የሀገር ውስጥ ተቋማት ያን ያህል የተደራጁ እንዳልሆኑ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ማቲዮስ ፤ እነዚህኞቹ የውጪዎቹን መምጣት በስጋት ሊመለከቱት ይችላሉ ብለዋል።


ነገሩ አይቀሬ መሆኑን ሲያውቁ ግን ከውጪዎቹ ጋር አብረው የሚሰሩበትን መንገድ መፈለጋቸው እንደማይቀር ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ውብሸትም የሚሻለው ራስን ለውድድር ብቁ አድርጎ መገኘት ነው ብለዋል።


የውጭ የጭነት አስተላላፊዎች በዘርፉ ገብተው እንዲሰሩ መንግስት አንድ ቀን መፍቀዱ ይጠበቅ ነበርም ብለዋል።


በኢትዮጵያ የጭነት ማስተላለፍ ስራ ለውጭ ባለሃብቶች ሙሉ በሙሉ ክፍት ሆኗል ቢባልም በጣም ትላልቅ የሆኑ ኩባንያዎች ላይመጡ ይችላሉ ሲሉም አቶ ዳዊት ግምታቸውን ተናግረዋል።


ከሌሎች ሀገራት አንጻር በኢትዮጵያ የሚጓጓዘው ጭነት መጠን ትላልቆቹን ኩባንያዎች ላይጋብዛቸው ይችላል ነው ያሉት።


መካከለኛ እና ከዚያ በታች የሆኑ ኩባንያዎች ግን ሊመጡ ይችላሉ ብለዋል።


እነሱም ቢሆኑ ግን ከሀገር ውስጥ የጭነት አስተላላፊዎች ጋር ተባብረው ለመስራት ፍቃደኛ ካልሆኑ ጉዳት መኖሩ አይቀርም ሲሉ አክለዋል።


ውሳኔው የጭነት አገልግሎት በሚሰጣቸው ተቋማት በኩልስ እንዴት ታይታል? የሚለውን ለማወቅ ፤ የኢትዮጵያ አበባ ፤ አትክልትና ፍራፍሬ ፤ አምራቾች እና ላኪዎች ማህበርን ጠይቀናል።


የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ በሰጡን ምላሽ መንግስት የንግዱን ከባቢ ምቹ ለማድረግ 140 ያህል የፖሊሲ ማሻሻያዎች እያደረገ እንደሚገኝ በመጥቀስ ፤የጭነት አስተላላፊነት ስራ ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት እንዲሆን የተላለፈው ውሳኔም የዚሁ አካል ነው ብለው እንደሚያምኑ ነግረውናል።


አዲሱ አሰራር ከቀናት በኋላ በሚጀምረው አዲሱ የበጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል ተብሏል።


የኢትዮጵያ የጭነት አስተላላፊዎች እና የሽያጭ ወኪሎች ማህበር (EFFSAA) በጭነት አስተላላፊነት፣ ሎጂስቲክስና ትራንስፖርት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎች የተቋቋመ ብሔራዊ ማህበር ነው፡፡


ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ…..

ንጋቱ ረጋሳ

1 Comment


镇华 莫
镇华 莫
Jul 03

Wow, Ethiopia's push to attract foreign investors is really exciting—great to see logistics and policies improving. Speaking of guides, if you ever need tips for gaming, check out the Kingshot Guide for strategies and gear advice. Keep up the awesome work!

Like
Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page