በኢራን ወታደራዊ እርምጃ ስለመውሰድ በአሜሪካ በኩል እየተነሳ ያለውን ሀሳብ ኢራን የምር አድርጋ ብትወስደው ይበጃታል ተባለ፡፡
- Feb 26
- 2 min read
የካቲት 19/2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች
በኢራን ወታደራዊ እርምጃ ስለመውሰድ በአሜሪካ በኩል እየተነሳ ያለውን ሀሳብ ኢራን የምር አድርጋ ብትወስደው ይበጃታል ተባለ፡፡
ይህንን ያሉት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዘዳንት ጄዲ ቫንስ ናቸው፡፡
ሁለቱ ሀገሮች በኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም ዙሪያ ለሶስተኛ ዙር ንግግር ጄኔቫ የገቡ ሲሆን ምክትል ፕሬዘዳንቱ ግን ኢራን አሁንም ለሰላማዊው መንገድ ዝግጁ አትመስልም እያሉ ነው፡፡
የኒውክሊየር ፕሮግራሟንም እንዳላቆመች መረጃ አለን ያሉት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ያ ለአሜሪካ ትልቅ ችግር ነው ብለዋል፡፡

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ደግሞ የዛሬው የጀኔቫ ስብሰባ በኢራን የኒውክሊየር እና የባለስቲክ ሚሳየል ፕሮግራሟ ዙሪያ ድርድር የሚደረግበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በኢራን በኩል ግን የሚሳየል ፕሮግራሙን የተመለከተው ሀሳብ ከአጀንዳው እንዲወጣ ፍላጎት እንዳላት አንስተው ያ ለአሜሪካ ትልቅ ችግር ነው ማለታቸውን አልጀዚራ አውርቷል፡፡
የጄኔቫው ስብሰባ ከመደረጉ አስቀድሞም አሜሪካ ከኢራን የነዳጅ ንግድ ጋር በተገናኘ እጃቸው አለበት ባለቻቸው 30 ግለሰቦች ድርጅቶችና መርከቦች ላይ ተጨማሪ ማእቀብ መጣሏም ተሰምቷል፡፡
በሶማሊያ 6.5 ሚሊዮን ህዝብ ለከፋ ርሀብ ሊጋለጥ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት አስጠነቀቀ፡፡
በአካባቢው የተከሰተው የተራዘመ ድርቅ የከፋውን ርሀብ ሊያስከትል ይችላል ብሏል፡፡
ጦርነትና የአለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ መቀነስ ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑንም ድርጅቱ መጥቀሱን አልጀዚራ አውርቷል፡፡
በሶማሊያ ድርቅና ግጭት በበረታባቸው አካባቢዎች ባለፈው አመት ብቻ ከ300 ሺህ በላይ ህዝብ ቀዬውን ጥሎ መሰደዱም ተነግሯል፡፡
እድሜያቸው ከ5 አመት በታች ያሉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ህፃናትም ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይጋለጣሉም ተብሏል፡፡
የከፋው አደጋ ከመምጣቱ በፊትም አለም አቀፉማህበረሰብ ርብርብ እንዲያደርግ የተባበሩት መንግስታት ጥሪ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡
በሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት የታሰሩ የሴኔጋል ደጋፊዎችን ለማስለቀቅ ሴኔጋል እላይ እታች እያለች ነው ተባለ፡፡
በውድድሩ ወቅት የታሰሩ 18 የሴኔጋል ደጋፊዎችን ጉዳይ እየተከታተሉት መሆኑን የሴኔጋሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦስማኔ ሶንኮ ተናግረዋል፡፡
ሴኔጋል በአሸናፊነት ባጠናቀቀችበት ውድድር ፍፃሜ ወቅት በተፈጠረው ሁከት ወደ ሜዳ የገቡ የሴኔጋል ደጋፊዎች በጊዜው ተይዘው መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት ደጋፊዎች ከሶስት ወር እስከ አንድ አመትና በገንዘብ ሊያስቀጣቸው የሚችል ክስ እንደሚመሰረትባቸው ተነግሯቸዋል ተብሏል፡፡
የሴኔጋሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁለት እራሳቸውን ወንድማማች እያሉ በሚጠሩ ሀገሮች መሀከል አንዲህ ዓይነት ነገር መፈጠር አልነበረበትም ማለታቸውን አልጀዚራ አውርቷል፡፡
የፍ/ቤቱ ክስ ውድቅ ተደርጎ በምህረት እንዲለቀቁም ለሞሮኮው ንጉስ ጥያቄ እናቀርባለን ብለዋል፡፡
ያም ካልተሳካ ግን በሁለቱ ሀገሮች መሀከል ባለው የእስረኞች ልውውጥ ስምምነት መሰረት ደጋፊዎቹ በሀገራቸው የእስር ጊዜያቸውን እንዲጨርሱ ይደረጋል ብለዋል።
በኢራን የኒውክሊየር እና የአቶሚክ መሳሪያ ፕሮግራም ዙሪያ የሚመክረው ሶስተኛው ዙር ድርድር ዛሬ በጄኔቫ ይደረጋል፡፡
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አስቀድመው ስዊዘርላድ ጀኔቫ መድረሳቸው ተነግሯል፡፡
በኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም ዙሪያ ድርድር ለማድረግ በተጠራው ስብሰባ ላይ እንዳለፉት ጊዜያት አሜሪካን የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የልጃቸው ባል ጃሬድ ኩሽነር ይወክላሉ መባሉን አልጀዚራ አውርቷል፡፡
የአሜሪካና የኢራን ባለስልጣናት ንግግር ሁለቱ ሀገራት ወደ ጦርነት ሊያመሩ ስለመሆኑ በስፋት እየተወራ ባለበት በዚህ ወቅት የሚደረግ ነው፡፡
በሁለቱም ሀገሮች በኩል አሁንም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለነገሩ እልባት መስጠት የሚቻልበት እድል እንዳለ እየተነሳ ነው፡፡
በአሜሪካ በኩል ኢራን የአቶሚክ እና የኒውክሊየር ፕሮግራሟን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጋ እንድትተው ፍላጎት አላት፡፡
ኢራን ግን ማሻሻያ ማድረግ እንጂ ሙሉ ለሙሉ መተው የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት የለውም እያለች ነው፡፡
በኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም ዙሪያ ኢራን እና አሜሪካ የሚያደርጉት ድርድር የዛሬው ለሶስተኛ ዙር የሚደረግ ይሆናል ያለው የመረጃ ምንጩ የመጀመሪያው በኦማን ሁለተኛው በቅርቡ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ መደረጉን ለትውስታ አንስቷል፡፡
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Website፡ https://www.shegerfm.com/
YouTube : https://shorturl.at/18TS1
Telegram : https://shorturl.at/68aeK
Facebook፡ https://shorturl.at/tm5Q4
WhatsApp : https://shorturl.at/8vwRx
LinkedIn: https://shorturl.at/Vfe6i
Tiktok : https://shorturl.at/lhYiv
Instagram: https://shorturl.at/9X4S7





Comments