top of page

በሌላ ሰው የመሬት ይዞታ ላይ ባለይዞታው ፈቅዶለት ቤት የሰራ ሰው የቤቱ ባለቤት ይሆናል የሚለውና ፍርድ ቤቶች እንደ አስገዳጅ ህግ ሲጠቀሙበት የቆየው ውሳኔ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም ተሻረ፡፡

  • Aug 5
  • 2 min read

ሐምሌ 29 2018


በሌላ ሰው የመሬት ይዞታ ላይ ባለይዞታው ፈቅዶለት ቤት የሰራ ሰው የቤቱ ባለቤት ይሆናል የሚለውና ፍርድ ቤቶች እንደ አስገዳጅ ህግ ሲጠቀሙበት የቆየው ውሳኔ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጉም ተሻረ፡፡


ከዚህ ቀደም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጠው በዚሁ አስገዳጅ ውሳኔ በስር ፍርድ ቤቶች ሲሰራበት የቆየው ድንጋጌ የተሻረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ 29 ቀን 2018 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባወ ባሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡


የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሰጣቸው የህግ ትርጉምን መሰረት ያደረጉ አስገዳጅ ውሳኔዎች በስር ፍርድ ቤቶች እንደ ህግ ሆነው የሚሰራባቸው ሲሆን በሌላ ሰው ይዞታ ላይ ባለቤቱ ፍቅዶለት ቤት የሰራ ሰው ንብረት እንዳፈራ ተቆጥሮ የቤቱ ባለቤት ይሆናል የሚል አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቶ ለፍርድ ቤቶች ውሳኔ በመሰረትነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡


የስር ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሲሰጡ የቆዩት ኢትዮጵያ የፍትሃብሔር ህግንም መሰረት ያደረገ ነበር።


በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 1779 (1) ባለ መሬቱ ሳይቃወም በሌላ ሰው መሬት ላይ ህንፃ የሰራ ሰው የዚሁ ህንፃ ባለቤት ይሆናል በሚል ይደነግጋል፡፡


ይሁንና በጉዳዩ ላይ የህገ መንግስት ትርጉም እንዲሰጥበት የተጠየቀው በፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አሰራሩ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ እንዲሻር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክረ ሀሳብ አቅርቧል፡፡


የህገ መንግስት ትርጉም በመስጠት የውሳኔ ሀሳቡን ለፌዴሬሸን ምክር ቤት ያቀረበው የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የህገ መንግስቱን አንቀፅ 40 (1) ጠቅሷል፡፡


በህገ መንግስቱ አንቀፅ 40 (1) መሰረት በመሬት ላይ ንብረት ያፈራ ሰው የንብረቱ ባለቤት ይሆናል የሚለው ድንጋጌ የሚሰራው የመሬት ባለ ይዞታ መብት ላለው እንጂ በሌላ ሰው ይዞታ ላይ ያለ ህጋዊ መሰረት ቤት ለገነባው ሰው የቤት ባለቤትነት መብት ለመስጠት አይደለም ብሏል፡፡


በመሆኑም ባለ ይዞታው ፈቅዶለት በመሬቱ ላይ ቤት የሰራ ሰው የሚኖረው መብት ወይም መጠየቅ የሚችለው የገነባበትን ወጭ ብቻ እንጂ የቤት ባለቤት ይሆናል በሚል በፍርድ ቤቶች ሲሰጥ የቆየው ውሳኔ ኢ-ህገመንግስታዊ በመሆኑ ሊሻር ይገባዋል ሲል የውሳኔ ሀሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርቧል፡፡


ምክር ቤቱም ባለፈው ሰኔ 29 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የውሳኔ ሀሳቡንም በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ እንዳፀደቀው ካወጣው ዝርዝር ውሳኔ ተመለክተናል፡፡


በመሆኑም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎ በሌላ ሰው መሬት ላይ ባለይዞታው ፈቅዶ ቤት የሰራ ሰው የቤቱ ባለቤት ይሆናል በማለት የሰጣቸው የቀደሙ አስገዳጅ ውሳኔዎች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሽረዋል፡፡


ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የሚሰጡት ውሳኔም ይሄንኑ የህገ መንግስት ትርጉም መሰረት ያደረገ ይሆናል ተብሏል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page