በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል 17ቱ በፌዴራል መስሪያ ቤቶች አንድም ሰራተኛ የላቸውም ተባለ።
ይህንን ያለው የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ነው።
በፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ታይቷል የተባለው ይህንን የአካታችነት ክፍተት ለማስተካከል፤ በተሻሻለው አዲሱ የፌዴራል የመንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶታል ተብሏል።
ብዙ ብሔር ብሄረሰቦች ባሉባት ሀገር በፌደራል ደረጃ ምንም የመንግስት ሰራተኛ የሌላቸው ብሔሮች ሊኖሩ አይገባም ብሏል ኮሚሽኑ።
እነዚህ በፌዴራል ደረጃ አንድም ሰራተኛ የላቸውም የተባሉ ብዛኞቹ በአሁን ወቅት ትምህርት እየተማሩ ስለሆነ በቀጣይ ቅጥር ሲፈጸም እነሱን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ይረዳል ተብሏል።
''በኢትዮጵያ ያሉ ብሔረሰቦች ቁጥር በተለምዶ ከ80 በላይ ሲባል ይሰማል፤ በትክክል ቁጥራቸው ስንት ነው?'' በሚል ከወራት በፊት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በፓርላማ አባላት ተጠይቆ፤ ''ብዙዎቹ ጋር የባህልና የቋንቋ መመሳሰል ስላላቸው እኔም ተቸግሬአለሁ'' ማለቱ የሚታወስ ነው።
በሌላ በኩል ተሻሽሎ የቀረበው የፌደራል የመንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ በፖርላማ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለውይይት በቀረበበት ወቅት ስለ መንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ጉዳይ በሰፊው ተነስቷል።
ይሁን እንጂ አሁን ተሻሽሎ የቀረበው ረቂቅ የደመወዝ ጭማሪን በተመለከተ ያካተተው አንቀጽ እንደሌለ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር) አረጋግጠዋል።
ስለ ደመወዝ ጭማሪ በዚህ ረቂቅ አይካተት እንጂ ከሚመለከታቸው ጋር እየተነጋርንበት ነውም ብለዋል ኮሚሽነሩ።
በአሁኑ ወቅት በመላው ሀገሪቱ በመንግሥት መስሪያ ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች በቁጥር 2.4 ሚሊየን ገደማ እንደሆኑ መረጃዎች ያስረዳሉ።
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments