top of page

ሰኔ 7፣ 2016 - በአዲስ አበባ በቅርቡ ወደ ስራ የገቡ የገበያ ማዕከላት በደላሎች የሚፈጠርን የዋጋ ንረት ማስቀረት ችለዋል ተብሏል

በአዲስ አበባ በቅርቡ ወደ ስራ የገቡ የገበያ ማዕከላት በደላሎች የሚፈጠርን የዋጋ ንረት ማስቀረት ችለዋል ተብሏል፡፡


በከተማዋ መግቢያ በሮች በተከፈቱት የገበያ ማዕከላት ከ160 በላይ አምራቾች መግባታቸውንና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በቀጥታ ከእርሻ ወደ ሸማቹ እያቀረቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለሸገር ተናግሯል፡፡


በለሚኩራ፤ ኮልፌና አቃቂ ቃሊቲ የሚገኙት የገቤ ማዕከላቱ ከ3 ወራት በፊት በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንደገቡ በቢሮው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሰውነት አየለ ነግረውናል፡፡


ወደ ገበያ ማዕከላቱ የገቡት ሁሉም ነጋዴዎች አመቱን ሙሉ እያመረቱ ለነዋሪው የሚያቀርቡ፣ዋጋቸውም ከመደበኛው ከ15 እስከ 20 በመቶ የቀነሰ ነው፡፡


የከተማ አስተዳደሩ በ6 ቢሊዮን ብር ወጪ እያስገነባቸው ካሉ 5 የገበያ ማዕከላት ወደ ስራ የገቡት 3ቱ ነዋሪውን ላስመረረው የኑሮ ውድነት ምን የፈየዱት ነገር አለ ስንል ላነሳንላቸው የገበያ ማዕከላቱ በደላሎች የሚፈጠርን የዋጋ ንረት በማስቀረት የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ በተቻለ መጠን አንዳንዱ እንዲቀንስ፣ መቀነስ ያልቻለው ደግሞ ባለበት እንዲቀጥል አድርጓል ይላሉ፡፡


በከተማዋ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሽንኩርትና ቲማቲምን ጨምሮ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ዋጋ መቀነስ ለማሳየቱ ዋናው ምክንያት ወደ ማዕከላቱ ምርቶች በገፍ መግባታቸው ነው ብለዋል፡፡


በማዕከላቱ የገቡ ነጋዴዎች በለጠፉት ዋጋ መሰረት መሸጥ አለመሸጣቸውን የንግድ ቢሮ ባለሙያዎችን መድቦ እየተከታተለ እርምጃ እንደሚወስድም አቶ ሰውነት ጠቅሰዋል፡፡


ምንታምር ጸጋው



Comments


bottom of page