top of page

ሰኔ 6፣ 2016 - የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የባንክ ስራን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አምስት መመሪያዎችን አሻሻለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በህግ በተሰጠው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት የፋይናንስ ዘርፉን ደህንነት እና መረጋጋት ለማስጠበቅ  እየሰራ ነው ብሏል፡፡


በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በስትራቴጂክ ዕቅዱ መሠረት አምስት የተሻሻሉ መመሪያዎችን ማሻሻሉን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ እወቁልኝ ብሏል፡፡


በመመሪያዎቹ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችንም ባንኩ ይፋ አድርጓል፡፡


በዚህም መሰረት ማንኛውም ባንክ ለአንድ ወይም ተያያዥነት ላላቸው ደንበኞች የሚኖረው አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት ከባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ከሀያ አምስት በመቶ (25%) እንዳይበልጥ ገድቧል፡፡


የመመሪያው ዓላማ አንድ ባንክ ተዛማጅነት ካላቸው አካላት ጋር በሚያደርገው ግንኑነት ብድር አግባብነት በሌለው መንገድ እንዳይሰጥ፣ እንዲሁም የጥቅም ግጭትን ለመቀነስ እንዲሁም ተዛማጅነት ካላቸው አካላት ጋር ባንኮች የሚያደርጉትን ማንኛውም ግብይት በተመለከተ በቂ ክትትል ለማድረግ እና ያለ አድልዎ በተገቢው መንገድ የተሰጠ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው ተብሏል።


ይህ መመሪያ በዋነኛነት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ገደቦች ጥሏል፡፡


በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባንክ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት በማንኛውም ጊዜ የሚኖረው አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት ከባንኩ ጠቅላላ ካፒታል ከ15% እንዳይበልጥ ገደብ ተጥሏል፡፡


በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባንክ ጋር ተዛማጅነት ላላቸው አካላት በሙሉ በማንኛውም ጊዜ የሚኖር አጠቃላይ የብድር ተጋላጭነት ከባንክ ጠቅላላ ካፒታል ከ35% እንዳይበልጥ ተገድቧል።


በተጨማሪም  አንድ ባንክ ተዛማጅ ከሆኑ ወገኖች ጋር ግብይት ሲፈጽም ከማናቸውም ተዛማጅ ካልሆኑ ወገኖች ጋር ግብይት ሲፈጽም ተግባራዊ በሚደረግ ሁኔታዎች ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልክ እንዲሆን እና ከዚህ በተለየ ሁኔታ እንዳይፈጸም ይደነግጋል።


ከባንኩ ካፒታል ከአምስት በመቶ (5%) በላይ የሆኑትን እና የውል ማሻሻያ የተደረገባቸውን ብድሮች አጠቃላይ መረጃ በየጊዜው ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርት እንዲደረግ ያስገድዳል።


አንድ ወቅቱን ጠብቆ መከፈል ያልቻለ እና ለተበላሸ ብድር የተቀመጠውን መስፈርት ያሟላ ብድር፣ ለብድሩ መያዣነት የቀረበው ዋስትና ምንም ይሁን ምን እንደ ተበላሸ ብድር ተወስዶ ወለድ የማይከፈልበት ምድብ ውስጥ መካተት እንደሚኖርበትም ተቀምጧል፡፡


አንድ ተበዳሪ ከአንድ ባንክ የተለያዩ ብድሮችን የወሰደ ከሆነ እና ከብድሮቹ አንዱ የተበላሸ ከሆነ ይህ የተበላሸው ብድር ባንኩ ለደንበኛው ከሰጠው አጠቃላይ ብድር ወይም ተጋላጭነት 20% እና ከዛ በላይ ከሆነ ሁሉም ብድሮች ወዲያውኑ በተበላሸ ብድር መደብ ውስጥ እንዲካተቱም ተደርጓል።


አንድ ብድር ምንም እንኳን የመክፈያ ጊዜው ያልደረሰ ቢሆንም በተለያዩ ክስተቶች እና ሁኔታዎች ሳቢያ ብድሩን በቀጣይ ለመክፈል የሚያስችል እድል የጠበበ እና የተመናመነ እንደሆነ አመላካች ሁኔታ ካለ፣ ብድሩ እንደ ተበላሸ ብድር ተቆጥሮ ቢያንስ “አጠራጣሪ ብድሮች” የሚል መደብ ላይ መካተት ይኖርበታልም ተብሏል፡፡


ብድርን ሁልጊዜ ጤናማ አስመስሎ ማቅረብን ለመከላከል ለባንክ በሚፈቀደው ከፍተኛ የብድር ውል የማሻሻል ድግግሞሽ መጠን ላይ ገደብ ጥሏል።


በዚሁ መሠረት ቀደም ሲል ለአጭርና ለመካከለኛ ጊዜ ብድሮች አምስት ጊዜ ይፈቀድ የነበረውን የማሻሻል ድግግሞሽ ከሦስት ጊዜ እንዳይበልጥ፤ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ብድር እስከ ስድስት ጊዜ ይፈቀድ የነበረው ድግግሞሽ ከአራት ጊዜ እንዳይበልጥ ደንግጓል፡፡


በዘርፉ በቦርድ ምርጫ ሂደት፣ በቦርድ ሹመት እና በአስመራጭ ኮሚቴዎች ተግባራት ላይ ለውጦች አድርጓል፤ አካታችነት እና ልዩነትን ለማስተናገድ ይቻል ዘንድ መመሪያው ቢያንስ ሁለት ሴቶች በቦርድ አባልነት የሚካተቱበትን አሰገዳጅ ድንጋጌ አካቷል፡፡


በመጨረሻም እነዚህን የወጡ መመሪያዎች ባንኮች በጥብቅ እንዲተገብሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አሳስቧል፡፡


መመሪያዎቹን ማሻሻል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት በሥራ ላይ ያለውን የባንክ ዘርፍ የቁጥጥር ሥርዓት ከዓለም አቀፍ መርሆዎች  እና ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲሁም የባንክ ዘርፍ ከደረሰበት ዕድገት ጋር የተጣጣመ በማድረግ ዘርፉ በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ እንዲሆን ለማስቻል ነው መባሉንም ሰምተናል፡፡


ምንታምር ፀጋው

Comments


bottom of page