የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ልጅ ሐንተር ባይደን በህገ-ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ በፌዴራል ተመራጭ ዳኞች ችሎት ጥፋተኛ ተባለ፡፡
ዋናው ጉዳይ ሐንተር ባይደን የአደገኛ እፅ ተጠቃሚ በነበረበት ወቅት ህጉ እየከለከለ ሽጉጥ ታጥቋል የሚል ነው፡፡
በግዢ ማረጋገጫ ሰነዱም ላይ ዋሽቷል በሚል በ3 ጭብጦች በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ መባሉን CNN ፅፏል፡፡
ሐንተር ባይደን ጥፋተኛ በተባለባቸው ጭብጦች እስከ 25 አመት የሚደርስ እስር እና ከ750 ሺህ ዶላር ያላነሰ የገንዘብ መቀጫ ሊፈረድበት ይችላል ተብሏል፡፡
ያም ሆኖ እንደመጀመሪያ ጊዜ ጥፋተኛ ከዚህ ቀለል ያለ ቅጣት ሊወስንበት እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የቅጣት ውሳኔው ከ3 ወራት በኋላ ሊሰጥ እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡
በዩክሬይን የ2ኛዋ ታላቅ ከተማ ሐርኪቭ ከንቲባ ከድንበር ማዶ የሚገኝን የሩሲያ የሚሳየል ማስወንጨፊያ ስፍራ አውድመናል አሉ፡፡
ከንቲባው የሚሳየል ማስወንጨፊያው ከተመታ በኋላ ከሩሲያ ድብደባ ፋታ አግኝተናል ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የሀርኪቭ ከተማ ከንቲባ አስተያየት የተሰማው ዩክሬይን ከዕራባዊያኑ በተሰጧት ታላላቅ መሳሪያዎች በሩሲያ ላይ ድንበር ተሻጋሪ ጥቃት እንድትፈፅም ተፈቅዶላታል ከተባለ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው፡፡
ሩሲያ ምዕራባዊያኑን ይሄ እርምጃ ከክፉ ያዳርሰናል ስትል ስታስጠነቅቃቸው ሰንብታለች፡፡
የዩክሬይን ሹሞች ድንበር አሻግረን የሩሲያን ሚሳየል ማስወንጨፊያ መትተና ቢሉም ሩሲያ በሐርኪቭ ግዛት ሁለት ተጨማሪ ስፍራዎችን ይዣለሁ ማለቷ ተሰምቷል፡፡
በዚህ ረገድ የዩክሬይን ሹሞች የሰጡት ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም፡፡
ሥርዓተ አልበኝነት በነገሰባት የካሪቢያኗ አገር ሔይቲ አዲስ መንግስት መመስረቱ ተሰማ፡፡
አገሪቱ በአብዛኛው በተደራጁ የወሮበላ ቡድኖች ተፅዕኖ ስር እንደሆነች ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሔነሪ በሮበሎቹ ግፊት ከመንፈቅ በፊት ስልጣን ለመልቀቅ ተገድደዋል፡፡
አሁን የሽግግሩ ምክር ቤት የአዲሱን መንግስት የካቢኔ አባላት መሰየሙ ተሰምቷል፡፡
ከ2 ሳምንታት በፊት በጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሾመው የነበሩት ጋሪ ኮኒል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
የአዲሱ መንግስት መሰየም በአገሪቱ ህግ እና ሥርዓትን ለማስፈን እንደ ታላቅ እርምጃ ተቆጥሯል፡፡
የኬንያው ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ በቅርቡ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የኬኒያ ፖሊሶች በሔይቲ መሰማራት ይጀምራሉ ማለታቸው ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡
ከኬንያ በተጨማሪ የፖሊስ ሀይሎቻቸውን ወደ ሄይቲ እንልካለን ያሉ ሌሎች ሀገሮችም አሉ፡፡
ሩሲያ የአጭር ርቀት ተምዘግዛጊ የኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ልምምድ እያደረገች ነው፡፡
የአሁኑ የታክቲካል የኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ልምምድ በጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ 2ኛው እንደሆነ ሬውተርስ ፅፏል፡፡
የአጭር ርቀት ተምዘግዛጊ የኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ልምምዱ 2ኛ ምዕራፍ እየተካሄደ ያለው ከቤላሩስ ጋር በጥምረት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ቤላሩስ የኒኩሊየር የጦር መሳሪያ ባለቤት አገር አይደለችም፡፡
ሆኖም በአገሪቱ የሩሲያ የአጭር ርቀት ተምዘግዛጊ ታክቲካል የኒኩሊየር የጦር መሳሪያዎች እንደተደገኑባት ይነገራል፡፡
ቤላሩስም ከምዕራባዊያን እና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት /ኔቶ/ አባል ከሆኑ ጎረቤቶቼ የጦር ስጋት አለብኝ ባይ ነች፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments