top of page

ሰኔ 5፣ 2016 - ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብን ለማስመለስ በሚል የወጣው ረቂቅ አዋጅ ስልክ ጠልፎ ክትትል ማድረግን ለመርማሪዎች የሚፈቅድ ነው

በህገ-ወጥ መንገድ ወይም ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብን ለማስመለስ በሚል የወጣው ረቂቅ አዋጅ የግለሰቦችን ወይም የተቋማትን ስልክና የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን ጠልፎ ክትትል ማድረግን ለመርማሪዎች የሚፈቅድ ነው፡፡


አስር አመት ወደ ኋላ ሂዶ ይሰራል የተባለው ይኸው ህግ በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ንብረት ለማስመለስ በሚደረገው ሂደት መርማሪዎች ማስረጃ ለማሰባሰብ ልዩ ክትትል ያደርጋሉ ይላል፡፡


በዚህም የተጠርጣሪን የባንክ ሂሳቦችን ሌሎችንም ተመሳሳይ ሂሳብ እንዲከታተሉ፣ የኮምፒውተር ሥርዓቶችን እና ሰርቨሮችን እንዲፈትሹ ፣ ፖስታን ፣ ደብዳቤን ፣ ፋክስን እንዲጠልፉ ፣ ስልክና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎቻችንም ጠልፈው ክትትል እንዲያደርጉ የሚፈቅድ ነው፡፡


እንዲህ ያለው የመርማሪዎች ክትትልና ልዩ የማስረጃ ማሰባሰብ ሒደት ደግሞ ፍርድ ቤት የምርመራውን አስፈላጊነት ሲፈቅድ የሚፈፀም እንደሆነ በረቂቁ አንቀፅ 11 ቢደነግግም መርማሪው አስቸኳይ ሁኔታ ካጋጠመው ለሚኒስትሩ ወይም እሳቸው ለወከሉ ግለሰብ በማስፈቀድ ብቻ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የንብረት ምርመራ ማድረግና ማስረጃ ማሰባሰብን ይፈቅዳል፡፡ 

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ምንጩ ያልታወቀን የግለሰቦች ገንዘብ እና ንብረት ለመመርመር የተጠርጣሪውን የኑሮ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ላይሆን ይችላል ተብሏል፡፡


ይህም ማለት ተጠርጣሪዎቹ እዚህ ግባ የሚባል ገቢ ባይኖቸውም በስሙ ያለው ንብረት በኑሮ ደረጃቸው ከሚያገኙት በላይ ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ልዩ ምርመራ ይካሄድበታል ይላል ረቂቅ ህጉ፡፡


ይህም የተካተተው ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ንብረታቸውን በቤት ሰራተኛቸው በጥበቃቸው ወይም ምንም ዓይነት ገቢ በሌለው ግለሰብ ስም ስለሚያስቀምጡ ነው የሚል ምክንያት ቀርቧል፡፡


የአንድ ግለሰብ ገንዘብ ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዳልተገኘ ተጠርጥሮ ምርመራ ሲደረግ የንብረቱን ህጋዊነት ለማስረዳት በማስረጃ የተደገፈ ማብራሪያ ማቅረብ ይጠበቅበታል ይላል ረቂቅ አዋጁ፡፡


ለምሳሌ ገንዘቡን በንግድ ያገኘሁት ነው ካለ ህጋዊ ታክስ ደረሰኝ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡


ህጋዊ ታክስ ከከፈለበት ውጭ ያለው ሀብት ግን ምንጩ ያልታወቀ ተብሎ ሊወረስበት እንደሚችልም በህጉ ሰፍሯል፡፡


በተመሳሳይ ምንጩን ሲያስረዳ ከውጭ የተላከልኝ ገንዘብ ነው የሚል ከሆነ ገንዘቡ በህጋዊ መንገድ በባንክ ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ስለመሆኑ የባንክ ደረሰኝ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡


እንዲህ ያለ ሥርዓት በመዘርጋት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ህጋዊ መስመሩን ተከትሎ እንዲፈፅም ሚና ይኖረዋል ተብሎም ታምኖበታል፡፡


ምንጩ ያልታወቀ ተብሎ የየግለሰቦችን ንብረትና ገንዘብ ለመመርመር መረጃ አለኝ ያለ ማንኛውም ሰው በሰጠው አሳማኝ ጥቆማ፣ ከመንግስት እና ከግል ተቋማት በሚሰጥ ጥቆማ መሰረትም ሊከወን እንደሚል ህጉ ያስረዳል፡፡


ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትም ጥቆማው ሊሰጥ ይችላል፡፡


በምርመራና ክስም ተመሰርቶ የግለሰቦች ገንዘብ ምንጩ ያልታወቀ እንደሆነ ከተረጋገጠ በመንግስት ይወረሳል ይላል ረቂቅ ህጉ፡፡


በተጨማሪም ግለሰቦች ለመርማሪዎች የንብረታቸውን ምንጭ የማስረዳት ግዴታ የተጣለባቸው ሲሆን ትብብር ካላደረጉ በወንጀል ያስቀጣል ተብሏል፡፡


ረቂቅ ህጉ ለፓርላማው የቀረበ ሲሆን ለዝርዝር ለይታ  ለሚመለከታው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page