top of page

ሰኔ 5፣ 2016 - መንግስት ከሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያንን የመመለስ ስራ እየሰራ ቢሆንም በህገወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ሰዎች ትንሽ አይደሉም

መንግስት ከሳውዲ አረቢያ እና ከሌሎችም ሀገራት ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ እየሰራ ቢሆንም በሌላ በኩል በህገወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ሰዎች ትንሽ አይደሉም፡፡


መንግስት ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር የመመለስ ስራውንም ውሃ ቅዳ ውሀ መልስ እያደረገበት መሆኑ ተነግሯል፡፡


ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር የመመለስ ስራውን የሚከውነው የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለት ወራት ለተጠጋ ጊዜ በተሰራው ስራ ከሳውዲ አረቢያ ይመለሳሉ ከተባሉት ኢትዮጵያውያን ግማሽ ያህሉን እንዲመለሱ አድርጌአለሁ ብሏል፡፡


በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገር ቤት የመመለሱ ስራ ባሳለፍነው ሚያዚያ 04 ቀን 2016 ዓ.ም መጀመሩን ተከትሎ በአራት ወራት ጊዜ 70 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ለማምጣት ታቅዶ በሁለት ወራት ውስጥ ከ43ሺህ በላይ የሚሆኑትን መመለስ ችለናል የሚሉት በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍ እና ክትትል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጄ ተግይበሉ በአጠቃላይ በ2016 ዓ.ም ወደ ሀገር ቤት የመጡ ኢትዮጵያውያን ከ95ሺህ በላይ ናቸው ብለዋል፡፡


ከሳውዲ አረቢያም ሆነ ከሌሎች ሀገራት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ወደ ሃገራቸው የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ሚኒስቴሩ ምን የተለየ ድጋፍ ይደረግላቸዋል? ሸገር የጠየቃቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል እና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍ እና ክትትል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደረጄ ተግይበሉ ይህንን ብለዋል፡፡


ተመላሾቹ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ስራ የመስራት ፍላጎት ማጣት፣ ወደመጡበት ሀገር ለመመለስ መፈለግ እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት በመመለሱ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥሙች ችግሮች ናቸው የሚሉት አቶ ደረጄ በተለይ ስራው ውሀ ቅዳ ውሀ መለስ እንዳሆንብን በህገወጥ መንገድ ተመልሰው የሚሄዱ እና አዲስ መንገደኞችን ለመቀነስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስራዎችን እየከወነ ነው ብለዋል፡፡


መንግስት 70 ሺ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ሀገራቸው እመልሳለሁ ማለቱ የተነገረ ሲሆን ለሁለት ወራት በተጠጋ ጊዜ ከግማሽ በላዩ ተመልሰዋል ተብሏል፡፡


ፋሲካ ሙሉወርቅ

Comments


bottom of page