ሰኔ 4 2017 - የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ግሽበትን በተመለከተ የሚያውጣው ሪፖርት ካለው የኑሮ ውድነት ጋር የማይጣጣም ስለሆነ በአግባቡ እንዲታይ የምክር ቤት አባል ጠየቁ፡፡የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ የተቋሙ መረጃ ታማኝ ነው ብሏል፡፡
- sheger1021fm
- Jun 11
- 1 min read

በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የኢዜማ አባል የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በርታ ህዝቡ በኑሮ ወድነቱ እየተቸገረ እንደሆነ ተናግረው በተለይ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሚያወጣው መረጃ በደንብ ቢታይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ተቋሙን የሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴ ቢያው ሲሉ የጠቆሙት ዶ/ር አብርሃም ምክንያቱም መሬት ላይ ያለውን መረጃ እንዴት እየወሰደው ነው የሚለውን ማወቅ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የምግብ ዘይት በዓመት ውስጥ ብቻ በስድስት መቶ ብር ነው የጨመረው ሲሉ የተናገሩት የምክር ቤት አባሉ የጤፍንም ዋጋ እናቃለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አጠቃላይ በእለት ተእለት የምንጠቀማቸው ለኑሮአችን የሚያስፈልጉ ሸቀጦች ያሉበትን ሁኔታ ህዝቡ ያውቀቃል እኛም እናውቃለን ብለዋል፡፡
ስለዚህ በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የኑሮ ግሽበቱ ቀነሶ በ2014 ዓ.ም የነበረ የዋጋ ንረት ከ34 ከመቶ ወደ 14 ከመቶ ወረደ ሊባል የሚችለው?
ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ተቋሙ በደንብ ቢታይ እና ታዓማኒነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ መገለጫዎቹን ቢሰጡን ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩን አቶ አህመድ ሽዴን ጠይቀዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በሰጡት ምላሽ በየትኛውም የኢኮኖሚ መመዘኛ ዋጋ ንረት እድገት ምጣኔው እየቀነሰ ነው የሚገኘው ብለዋል፡፡
አገልግሎቱም ከፍተኛ አቅም ያለው ነው ያሉት ሚኒስትሩ መረጃውም ታዓማኒ ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡
የዚህ የዋጋ ንረት መረጃም የተናጥል ሳይሆን የአጠቃላይ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አህመድ ሽዴ በእያንዳንዱ ቀን የአንድ ግብዓት ዋጋ ሳይሆን የምግብ ነክም፣ ምግብ ነክ ያለልሆኑትም የአጠቃላይ የሁሉም ድምር ነው ብለዋል፡፡
በዚህም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት እድገት ሂደቱ በሁሉም የኢኮኖሚ መመዘኛ እየቀነሰ ለመሆኑ አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል ፡፡
የኑሮን ጫናን ለመቋቋም መንግስት የሰጣቸው ድጎማዎች ፣ባለፉት ዓመታት ሲሰራ የነበረው የግብርና ምርታማንት ፣ የእድገት ምንጮችን ማስፋታችን ፣ የግሉን ዘርፍ በኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ ማሳደጋችን እና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወጤታማነት ማሻሻል ላይ የሰራናቸው ስራዎች የዋጋ ግሽበትን በመቋቋም ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ተወጥቷል ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Comments