ሰኔ 4 2017 - በምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው ህወሃት እና የፌዴራሉ መንግስት ግንኙነት ከዚህ በኋላ ምን መልክ ሊይዝ ይችላል?
- sheger1021fm
- Jun 11, 2025
- 2 min read

ከሃምሳ ዓመት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የጎላ ሚና ይዞ የቆየው ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ / ህወሐት / በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲነት ተሰርዟል።
ቦርዱ ህወሃትን ከፖለቲካ ፓርቲነት የሰረዘው ተግብራቸው ያልኩትን የእርምት እርምጃዎች ባለመፈጸሙ ነው ብሏል።
ህወሃት በበኩሉ የቀደሙትም ሆኑ የአሁኑ የምርጫ ቦርድ ውሳኔዎች ትክክል አይደሉም ባይ ነው።
አለመግባባቶችን መፍታት ያለብን የሰሜኑን ጦርነት ለማስቆም ከፌዴራሉ መንግስት ጋር በፈረምነው የፕሪቶሪያው ስምምነት እንጂ በምርጫ ቦርድ ውሳኔዎች አይደለም የሚል አቋቋም አለው።
ውሳኔውን ተከትሎ በፌዴራል መንግስቱ እና በህወሃት መካከል ልዩነቱ መስፋት የጀመረ መስሏል።
ህወሃት ግንቦት 9 ቀን 2017 ባወጣው መግለጫ የፌዴራል መንግስት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በጣሰ መልኩ ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እያካሄደ ነው ሲል ከሷል።
ለመሆኑ በምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው ህወሃት እና የፌዴራሉ መንግስት ግንኙነት ከዚህ በኋላ ምን መልክ ሊይዝ ይችላል?
ሁለት መሠረታዊ ክስተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያሉን የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ በፀሎት አዲሱ ናቸው።
የመጀመሪያው እሳቸው እንደሚሉት ህወሃት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በፊት እንደነበረው በሌሎች ዕውቅና ያልተሰጠው ግን ራሱን እንደቻለ ሃይል ሊንቀሳቀስ ይችላል።
ህወሃት ትግራይ ላይ በርከት ያለ ደጋፊ እንዳለው የሚጠቅሱ ሰዎች አሉ።
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥም ተጽዕኖው ቀላል እንዳልሆነ ያነሳሉ።
በታጠቀው የክልሉ ሃይል ውስጥም ያለው ድጋፍ ሰፋ ያለ እንደሆነ ይጠቀሳሉ።
እነዚህ እና መሰል ጉዳዮች ተደማምረው ሁለቱ ዳግም ወደ ጦርነት ሊገቡ የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይችላል የሚሉ ተንታኞች አሉ።
የፖለቲካ ሣይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ በፀሎት አዲሱም በሁለቱ መካከል ጦርነት ሊነሳ የሚችልበት ዕድል ጠባብ ቢሆንም ፈጽሞ ዝግ አይደለም ይላሉ።
ሊፈጠሩ ይችላሉ ካሏቸው ሁለት መሰረታዊ ክስተቶች አንደኛው ይኸው እንደሆነም ነግረውናል።
የፌዴራል መንግስት አንዳንድ ጉዳዮች ሌተና ጀነራል ታደሰ ወረደ በሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል እንዲፈጸሙ ፍላጎቱን አሳይቷል።
ለአብነትም ጀኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው ሲሰየሙ በፈረሙት የተልዕኮ አፈጻጸም ቃል ኪዳን ሰነድ ላይ የሰፈረው አንዱ ጉዳይ ከህገ መንግስታዊ ፤ ከህጋዊ ስርአት ፤ ከሀገር ሉዓላዊነት ከፕሪቶሪያው ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ የሚል ነው።
ከሰሞኑ ደግሞ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በኩል ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ በተከለከሉ የጭነት መኪናዎች ዙሪያ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ጋር በተደረገ ውይይት ተሽከርካሪዎቹ ወደ ትግራይ እንዳይገቡ የተከለከሉት ሸቀጦቹ በህገ ወጥ መንገድ የክልሉን ድንበር ተሻግረው እየተሸጡ እንደሆነ በፌዴራል መንግስት በኩል መነገሩ እና ጉዳዩ በጋራ ኮሚቴ ተጣርቶ ማስተካከያ እንዲደረግ ከስምምነት መደረሱ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል መነገሩ እንዲሁ የሚታወስ ነው።
ከንግግሩ በኋላ ክልከላው ተነስቶ መኪኖቹ ወደ ትግራይ መግባት መጀመራቸው ተሰምቷል።
ጥያቄው ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፌዴራል መንግስት ጋር የሚደርሳቸውን እነዚህን እና መሰል ስምምነቶችን ምን ያህል የማስፈጸም አቅም ይኖረዋል? የሚል ነው።
ይህንኑ ለመጠየቅ ወደ ትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ የስራ ሃላፊዎች በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ለጊዜው ምላሸ ማግኘት አልቻልንም።
የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ በፀሎት አዲሱ ግን የጊዜያዊ አስተዳደሩ አቅም ያን ያህል ጠንካራ አይመስለኝም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ህወሃት አሁንም ከፍ ያለ ድርሻ እንዳለው የሚናገሩት አቶ በፀሎት አንዳንዶቹ የሁለቱም መሆናቸውንም ማስታወስ ይገባል ባይ ናቸው።
በፌዴራል መንግስት እና በህወሃት መካከል የሚኖረው አለመግባባት በፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት አፈጻጸም ላይም ተፅዕኖ ሊያመጣ እንደሚችልም ተነግሯል።
ንጋቱ ረጋሣ












Comments