በኢትዮጵያ ጉልበተኛ ያፈናቀላቸው፣ ተፈጥሮ ጨክና ያፈናቀለቻቸው በሌላም ምክንያቶች ከሞቀ ጎጆአቸው ወጥተው እርዳታ ጠባቂ ሆነው በየመጠለያው የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አሉ፡፡
ተፈናቃዮችን ለመጠበቅ ያግዛል፤ አፈናቃዩንም ለመጠየቅ ይረዳል በሚል ሀገሪቱ የካምፓላው ስምምነት ተብሎ የሚጠቀስን ስምምነት ከተቀበለች ቆየች፡፡
ግን ስምምነቱ ህግ ሆኖ አልወጣም፤ ለምን?
ይህ ህግ ጸድቆ ተግባራዊ ባለመሆኑ፤ ተፈናቃዮች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅሞች እያገኙ አይደለም ይህ ብቻ ሳይሆን አፈናቃዩና ጉዳት አድራሹ ተጠያቂ እየሆኑ አይደለም፡፡
ስምምነቱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አስፈላጊ የሆነ ጥበቃ እንዲደተረግላቸውና ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው የሚያስገድድ ህግ በውስጡ ይዟል፡፡
በተጨማሪም ከአንድ ቦታ በግጭትም ይሁን በተፈጥሮ አደጋ ቀያቸው ለቀው የተፈናቀሉ ሰዎች ከተቻለ ወደነበሩበት መመለስ እሱም በእነሱ ፍቃደኝነት ላይ ተመስርቶ መሆን አለበት ይላል፡፡
ሌላኛው ደግሞ ተፈናቅለው የሄዱበት ማህበረሰብ ጋር አብረው ተዋህደው እንዲኖሩ ማድረግና ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ የሚለው ይገኝበታል፡፡
ታዲያ ኢትዮጵያ የተቀበለችው አለማቀፍ ስምምነት በፓርላማ አፅድቃ ወደ ትግበራ ለመግባት ምን ያዛት?
የሰላም ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ህጉ ላይ የሚመለከታቸውን አካላት ተወያይተው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ተልኳል ያለ ሲሆን በፓርላማ እንዲጸድቅና ተግባራዊ እንዲደረግ እየተጠባበቅኩ ነው ብሏል፡፡
ማርታ በቀለ
Comments