ሰኔ 3 2017 - ኢትዮጵያ በጁቡቲ በኩል የምታስገባው ነዳጅ ከመርከብ ከመራገፉ በፊት ኤስ ጂ ኤስ በተባለ ዓለም አቀፍ ኩባንያ የጥራት ፍተሻ እንደሚደረግለት የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ተናገረ።
- sheger1021fm
- Jun 10
- 2 min read

ጁቡቲ ላይ ላብራቶሪ ስለሌለ የጥራት ማረጋገጡ ስራ የሚከናወነው ወደ ኬንያና ሌሎች ሀገራት እየተላከ ነው በሚል ትሬድ ማርክ አፍሪካ በሚሰኝ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ለሸገር የተሰጠው መረጃ ስህተት እንደሆነም ድርጅቱ ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ከውጪ የምታስገባው ነዳጅ ጭነት ላይ እያለ እና ሲራገፍ እንዲሁም ከሁለቱም ቦታዎች የሚወሰደው ናሙና፤ በነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በሚገኝ ላብራቶሪ ፍተሻ እንደሚደረግለት የመስሪያ ቤቱ የነዳጅ ጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ሃላፊ አቶ ስዩም አራጋው ተናግረዋል።
ነዳጁ ጁቡቲ ላይ ከመራገፉ በፊት ፍተሻውን የሚያካሂደው መቀመጫውን በዱባይ ያደረገና ኤስ ጂ ኤስ የተባለ አለም አቀፍ ኩባንያ መሆኑንም ነግረውናል።
ፍተሻው ከሠላሣ እስከ አርባ አምስት ደቂቃ በሚሆን ጊዜ የሚጠናቀቅ እንደሆነ አመልክተዋል።
ጁቡቲ ወደብ ላይ ነዳጅ ከመራገፉ በፊት የጥራት ፍተሻ ማድረግ የሚያስችል ላብራቶሪ ስለሌለ ናሙናው ወደ ኬንያና ሌሎች ሀገራት እየተላከ ጥራቱ እንደሚረጋገጥ መዘገባችን ይታወሳል።
በአፍሪካ የንግድና ሎጂስቲክስ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በሚሰራው እና ትሬድ ማርክ አፍሪካ በተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ እውነቱ ታዬ በኩል ለሸገር የተሰጠው መረጃ ስህተት መሆኑንም ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
አቶ እውነቱ ጥራቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል ላብራቶሪ ባለመኖሩ ድሬደዋ ላይ የመሰረተ ልማት ዝርግታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነበር ለሸገር የተናገሩት።
በትሬድ ማርክ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዝና ድርጅት ጋር ትብብር እየተዘረጋ ላለው ለዚህ መሰረተ ልማት 1 ነጥብ 6 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደተመደበም ጠቅሰው ነበር።
በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ሃላፊ አቶ ስዩም አራጋው ግን ኤስ ጂ ኤስ የተባለና አለም አቀፍ የፍተሻ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ስራውን ጁቡቲ ላይ እየሰራ እንደሚገኝና ወደ ኬንያም ሆነ ወደ ሌላ ሀገር ለፍተሻ በሚል የሚላክ የነዳጅ ናሙና የለምም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተቀጠረው ኤስ ጂ ኤስ ለሌሎች ሀገራት ጭምር የነዳጅ ጥራት ፍተሻ የሚያደርግ ተቋም እንደሆነ አቶ ስዩም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዝና ድርጅትና በትሬድ ማርክ አፍሪካ ትብብር ድሬደዋ ላይ ይገነባል ስለተባው ላብራቶሪም አቶ ስዩም አንስተዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ለኤስ ጂ ኤስ በውጪ ምንዛሪ የሚከፈለውን ገንዘብ ለመቀነስ በአማራጭነት እንዲደራጅ የተወሰነ ነው።
የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅትም ላብራቶሪው ድሬደዋ ላይ እየተገነባ ስለመሆኑ አረጋግጦልናል።
ንጋቱ ረጋሣ
Comentários