ሰኔ 3 2017- በአገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት መኖሩ ቢነግርም ለተቋማት የሚከፋፈሉ መድኃኒቶች በቂ ናቸው ቢባሉም አሁንም የአንዳንድ መድሃኒት አቅርቦት ችግር እንዳለ ተጠቃሚዎች ይናገራሉ፡፡
- sheger1021fm
- Jun 10
- 1 min read

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት በበኩሉ ይህንን ለማስቀረት ከመንግስት የጤና ተቋማት በተጨማሪ ለግሎቹም የማቀርብበትን አሰራር ዘርግቻለሁ ብሏል፡፡
በመንግስት የጤና ተቋማት ላይ በብዛት የሚገኙ ነገር ግን በግል እጥረት ያሉባቸው መድኃኒቶችን ለይቶ በማቅረብ የሚነሳውን የመድኃኒት ጥያቄ ለመመለስ እየሰራሁ ነው ሲል ተናግሯል፡፡
በሚነሳው የመድኃኒት እጥረት ጥያቄ ሳቢያ በመንግስት ተቋማት 200 እና 300 ብር የሚሸጡ እንደ ስኳር ያሉ መድኃኒቶች በግል ተቋማት ላይ እስከ 1000 ብር እንደሚሸጡና ይህንንም ለማስቀረት በቂ መጠን ያላቸው እንደ ኢንሱሊን ያሉ መድኃኒቶች ለግል ተቋማትም ለማቅረብ እንደሚሰራ የነገሩን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ናቸው፡፡
በግል የጤና ተቋማት ላይ በብዛት ፍላጎት ያሉባቸውን መድሃኒቶች የሚጠቅሙ ከሆነ ክፍት አድርገናል አሁንም አዲሱ ተቋሙ መመሪያ እንዲሁም በቅርቡ የጸደቀው አዋጅ የመድሃኒት አቅርቦቱ የሁሉንም ማህበረሰብ ያማከለ መሆን ስላለበት ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የሀገር ቤት የመድኃኒት ምርቱ መጠን መጨመሩን እና ይህም ረጅም ጊዜ የሚወስደውን የግዥ ሒደት በመቀነስ እዚሁ በመሸፈን በአቅርቦት ላይ የሚነሳውን ቅሬታ ለማስተካከል የሚያግዝ ነው ብለዋል ዶ/ር አብደልቃድር፡፡
የሀገር ቤት የመድሃኒት ምርቱ የዛሬ ሶስት አመት ከነበረበት 7 በመቶ አሁን ወደ 37 በመቶ አድጓል፤ በአገር ውስጥ አምራቾች የሚቀርቡ መድሃኒት አይነቶች በዘንድሮ አመት እንኳን 97 ደርሰዋል ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም በሀገር ቤት ያሉ አምራቾች ሲያነሱት የነበረው የውጭ ምንዛሪና የግብዓት ጥረት ቢስተካከልላቸውም 60 በመቶውን የመድኃኒት አቅርቦት ከሀገር ቤት አምራቾች ለመተካት ቢታሰብም አቅማቸው ጥቂት በመሆኑ ምርታቸው ከሃያ እና 30 በመቶ አላለፈም ከዚህ በላይ እንዲያምርቱ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
በሀገር ቤት አምራቾች የሚመረቱ መድሀኒቶችን ከውጪ ሀገር አቅራቢዎች መግዛት የተከለከለ በመሆኑም የምርት አቅማቸውን ማሳደግ አለባቸው ተብሏል፤ ከዚህ ቀደም ከውጪ ሀገራት ይገዙ የነበሩት እንደ ሰርጂካል ጓንት፣ስሪንጅና ጎዝ ሙሉ በሙሉ በሀገር ቤት መመረት መጀመራቸውንም ሰምተናል፡፡
ምህረት ስዩም
Comments