top of page

ሰኔ 28 2017 - የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ

  • sheger1021fm
  • 4 days ago
  • 2 min read

ዘረኝነት እና ጽንፈኝነትን ሲያስፋፉ የነበሩት፤ በህጋዊ መንገድ በፖለቲካ ፓርቲ ስም ተመስርተው እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ ይህንን የሚከለክል ድንጋጌም፤ ተሻሽሎ ለፓርላማው በቀረበው የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ እንዲካተት የምክር ቤት አባል ጠየቁ፡፡


የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ ፓርቲ አባሉ እና የምክር ቤት አባሉ አብርሃም በርታ(ዶ/ር) ይህን የጠየቁት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በትናንትናው እለት ከሰዓት በኋላ የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅን ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በመራበት ወቅት ነው፡፡

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁን መግለጫ በንባብ ያቀረቡት ዋና አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ቦርዱ ስልጣን እና ተግባሩን በተሻለ አቅም ለመፈጸም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የአስተዳደር ስራዎች ላይ ያሉ የህግ ከፍተቶችን ለማስተካከል የቀድሞውን አዋጅ ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል፡፡


በረቂቁ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡት የምክር ቤት አባሉ አብርሃም በርታ(ዶ/ር) በስራ ላይ ባለው አዋጅ ላይ የፓርቲዎችን አመሰራረት በአግባቡ እንደሚተነትን ተናግረው በተደጋጋሚ የሚነሱ መታየት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡


አሁን ኢትዮጵያ ከደረሰችበት ሁኔታ አንፃር የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ዓይነት ሁኔታ መከተል እንዳለባቸው እና አመሰራረታቸው በደንብ ቢታይ ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡


በተለይ ፓርቲዎች የሀገሪቱን አንድነት ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸው የተቆሙት የምክር ቤት አባሉ ብሔራዊ አንድነታችን፣ ሉዓላዊንታችን የሚያጠናክሩ ፓርቲዎች መመስረት አለባቸው የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


የእኛ ሀገር ፖለቲካ ፓርቲዎች ምን እየሰሩ እንደሆነ ይታወቃል ሲሉ የተናገሩት አብርሃም በርታ(ዶ/ር) ፕሮግራማቸው፣ ፖሊሲያቸው ምንድነው? ሲሉ ጠይቀው ባለፉት ጊዚያት እዚህ ቤት መነገር የሌለባቸው ለእኛም ትልቅ ፈተና የሆኑ ብዙ ችግሮችን አይተናል ብለዋል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲ ስም ተመስርቶ ማህበረሰብን እርስ በእርስ ማጋጨት፣ ጽንፈኝነትን፣ ዘረኝነትን፣ መከፋፈልን ሲያስፋፉ የነበሩት በህጋዊ መንገድ በፖለቲካ ፓርቲ ስም ተመስርተው ነው፤ አሁንም ከቁስላችን ጋር አየሸፋፈንን መሄድ የለብንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡


በመሆኑም በማሻሻያው ይህ እንዲከለከል ጠይቀዋል፡፡


ሌላው የምክር ቤት አባል አቶ ገነነው ገደቦ ረቂቅ አዋጅ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ምርጫ ከተካሄደ በኋላም በድህረ ምርጫ ወቅት የሚከሰቱ ችግሮች ስላሉ ቦርዱ ይህን ችግር ሊፈታ የሚችል ስልጣን እንዲኖረው ማድረግ ቢችል ሲሉ ሃሳብ ሰጠተዋል፡፡


በትናንትናው እለት በሙሉ ድምጽ ለዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመራው የህጉ የማሻሻያ ረቂቅ በብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል ግጭት እና አለመተማመንን የሚፈጥሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምርጫ ቦርድ እንዲሰርም በማስቻል መፍትሄ የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡

ያሬድ እንዳሻው ያዘጋጀውን በፋሲካ ሙሉወርቅ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Commenti


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page