ሰኔ 28 2017 - የአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የህይወት መርሆች ላይ የሚያተኩረው መፅሀፍ ከአንድ ወር በኋላ ለንባብ ይበቃል ተባለ
- sheger1021fm
- 4 days ago
- 2 min read
የአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የህይወት መርሆች ላይ የሚያተኩረው "Dissecting Haile" (የኃይሌ ኃይሎች) መፅሀፍ ከአንድ ወር በኋላ ለንባብ ይበቃል ተባለ።
የረጅም ርቀት ሯጭ እና ስራ ፈጣሪው የአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ስኬቶች ጀርባ ያሉ ሚስጥሮችን ያካተተ መጽሐፍ በልጁ ሜላት ኃይሌ ተዘጋጅቷል።
መጽሐፉ የረጅም ርቀት ሯጭ እና ስራ ፈጣሪው የአትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ የህይወት መርሆች እንደሚዳስስ በዛሬው እለት በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነግሯል።
ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፉ ስለ ሃይሌ ገብረስላሴ የሕይወት ፍልስፍና፣ ከኃይሌ ገብረስላሴ ስኬቶች ጀርባ ያሉ ሚስጥሮችን ያካተተ መሆኑ ተነግሮለታል።
መፅሀፉ የኃይሌ የጥንካሬው መሰረት ወይም መርሆች ምንድናቸው የሚለውን በ12 ምዕራፎች፣ በ247 ገፆች መዘጋጀቱ ተነግሯል።
#Dissecting_Haile (የኃይሌ ኃይሎች) መፅሀፍን የፃፍኩት ኃይሌ በሩጫም በቢዝነስም ስኬቱ የተከተላቸው መርሆቹ ትውልዱ ሊጠቅሙ ይችላሉ በሚል እንደሆነ ፀሀፊዋ ተናግራለች።

"ይህ መጽሐፍ ከኃይሌ ታላቅነት ጀርባ ያለውን ዘመን የማይሽረው መርሆች፤ እንደ አትሌት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ከሌሎች ታላላቅ መሪዎች ታሪክ ጋር የተዋሃደ ነው፤ የታላቅነትን ማንነት የሚገልጥ ነው፤ ይሀም ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን በሁላችንም ውስጥ እንደሚኖር ያሳያል" ብላለች ሜላት ኃይሌ።
በመፃህፉ በጣም ደስተኛ መሆኑን የተናገረው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ "ለብቻ ስኬታማ መሆን አይቻልም የእኔ ስኬት ከቤተሰቦቼ ፣ ከትዳር አጋሬ፣ አሰልጣኞቼ፣ ክለቤ ሌሎችም አስተዋጽኦ አበርክተዋ’’ል ሲል ተናግሮ አመስግኗል።
የ27 ጊዜ የአለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ መፅሀፉን የሚያነቡ ሰዎችም ‘’ኃይሌ ጎበዝ ነው እንዲሉ ሳይሆን እኔም እንደሱ ስኬታማ መሆን እችላለሁ ብለው እንዲያስቡ ነው’’ ሲል አስረድቷል።
"Dissecting Haile" (የኃይሌ ኃይሎች) መጽሐፍ የፊታችን ነሐሴ 2017 ዓ.ም በይፋ የሚለቀቅ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ማስጀመሪያ ዝግጅት፣ በመቀጠልም አለም አቀፍ ደረጃ ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ተነግሯል።
መፅሀፉ በኤሌክትሮኒክ አማራጮችና በሀርድ ኮፒ ከነሐሴ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በትዕዛዝ ለአንባቢያን ይቀርባል ተብሏል።
ስለዚሀም በአማዞን፣ በቴሌብር፣ በተለያዩ የኦንላይን አማራጮችና በመጽሐፍት መሸጫ መደብሮች በትዕዛዝ ማግኘት ይቻላል ሲባል ሰምተናል።
ለጊዜው ''Dissecting Haile'’ በሚል ርዕስ ለህትመት የሚበቃው መፅሀፋ ወደፊት ወደ አማርኛ እንዲሁም በብሬል እንደሚፃፍና እንደሚተረጎም ተነግሯል።
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Kommentarer