ሰኔ 28፣ 2016 - የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር በመሆን ላለፉት 5 ዓመታት ያገለገሉት ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) የአገልግሎት ጊዜያቸው ማብቃቱን ተናገሩ
- sheger1021fm
- Jul 5, 2024
- 1 min read
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር በመሆን ላለፉት 5 ዓመታት ያገለገሉት ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) የአገልግሎት ጊዜያቸው ማብቃቱን ተናገሩ፡፡
ዶ/ር ዳንኤል ይህንን የተናገሩት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ ከሰኔ 2015 እስከ 2016 ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡

በአዋጁ መሰረት፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና ኮሚሽነር እስኪሰይም ድረስ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው በማገልገል ላይ ያሉት ራኬብ መሰለ የሀላፊነቱን ቦታ ይረከባሉ ተብሏል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፤ ታገሠ ጫፎ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለን(ዶ/ር) ማሰናበታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው ሰኔ 25 ቀን 2011 ዓ.ም መሾማቸው ይታወሳል፡፡

ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በአለም አቀፍ ህግ የዶክትሬት ዲግሪ ያገኙት ዶክተር ዳንኤል በተለያዩ መንግስታዊ እና አለም አቀፍ ድርጅቶች ከሰብአዊ መብት ጉዳይ ጋር በተያያዘ አገልግለዋል፡፡
በአፍሪካ የአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር፣ በህብረት ኢንሹራንስ የህግ ክፍል ዋና ዳይሬክተር፣ በኢትዮጵያ የአክሽን ኤይድ የጥናትና ምርምር ሃላፊ በመሆንም ሰርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በኦክስፋም፣ በፓክት፣ ዩ ኤስ ኤይድ እና የአለም ባንክ በተሰኙ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ አማከረዋል፡፡
ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ዴሞክራሲን፣ የሕግ የበላይነትን፣ ሰብአዊ መብቶችን፣ መቻቻልን እና እኩልነትን በማስፋፋት ረገድ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰዎች” የሚሰጠውን የአውሮፓ ኅብረት ሹማን ሽልማት (Schuman EU Awards) በቅርቡ ተበርክቶላቸዋል።
ያሬድ እንዳሻው
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments