top of page

ሰኔ 28፣ 2016 - የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተጠናቀቀ ቢሆንም በንጹሃን ላይ የሚፈፀመው እስራትና የመንቀሳቀስ ገደብ ሙሉ በሙሉ አለመቆሙን ኢሰመኮ ተናገረ

በሀገሪቱ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተጠናቀቀ ቢሆንም በንጹሃን ላይ የሚፈፀመው እስራትና የመንቀሳቀስ ገደብ ሙሉ በሙሉ አለመቆሙን ኢሰመኮ ተናገረ፡፡


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ከሰኔ 2015 እስከ 2016 ዓ.ም ያለውን ዓመታዊ የሠብዓዊ መብቶች ሪፖርት ሲያቀርብ ነው ይህን ያለው፡፡


ግጭት ካለባቸው የአማራና የኦሮሚያ ክልል ውጪ አፋር፣ ሶማሌ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በርካታ ሰዎች ለመፈናቀል፣ ለአካል መጉደል እና ለሞት መዳረጋቸውን ሪፖርቱን ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት በዛሬው ዕለት የአገልግሎት ጊዜያቸው ማብቃቱን የተናገሩት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) ናቸው፡፡


በንጹሃን ላይ የሚፈፀሙ ከህግ ውጪ ግድያዎች፣ እስራቶች እና መፈናቀሎችም አሳሳቢ ሆነው መቀጠላቸውን ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡


በሀገሪቱ በርካታ አካቢዎች የመንቀሳቀስ መብት አደጋ ላይ ወድቋል ያሉት ኮሚሽነሩ በአዋጁ ወቅት በርካታ ሰዎች ያለ ኮማንድ ፖስት ትዕዛዝ ሲታሰሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡

የአዋጁን ማብቃት ተከትሎም የተወሰኑ ሰዎች የተለቀቁ ቢሆንም በንጹሃን ላይ የሚፈፀሙ ከህግ ውጪ ያለው እስራት ግን እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡


ከባለፉት ዓመታት ለኮሚሽኑ የቀረቡ አቤቱታዎችን መጨመራቸውን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ አስረድተዋል፡፡


በአጠቃላይ በሕይወት የመኖር መብት እና የመንቀሳቀስ መብት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ያሉት ኮሚሽነር ዳንኤል ይህም መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡


በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት በሀገሪቱ ባለው ግጭት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀዋል ያሉት ኮሚሽነሩ ይህንም የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡


በአጠቃላይ ለእነዚህ ሁሉ ምክንያት የሆነው ግጭት እንዲቆም ኮሚሽነሩ ጠይቋል፡፡


የባለፉት 5 ዓመታት የኮሚሽኑን ችግሮቶችና መልካም ጎኖች የተጠየቁት ኮሚሽነር ዳንኤል በግጭትና በግጭት አውድ ውስጥ የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡


ጠንካራ የሰብአዊ መብት መቋቋም እና የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ መፅደቁ በመልካም ጎን የሚጠቀስ መሆኑን ኮሚሽነሩ ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


Commentaires


bottom of page