top of page

ሰኔ 28፣ 2016 - የት/ት ጥራት ችግር ለመፍታት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ ያሉ፤ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ባለሀብቶች አንድ ላይ ሆነው ‘’አማና ሞዴል 2ኛ ደረጃ ት/ቤት’’ አቋቁመዋል

በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓቱ መውደቁ በውጤቱ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡


ይህን የትምህርት ጥራት ችግር ለመፍታት የፖሊሲ ማሻሻያ ቢደረግም ለውጡ ግን ገና መታየት አልጀመረም፡፡


የቤት ስራዎቹም ብዙ መሆናቸው ዘረፋን የሚያውቁት ያስረዳሉ፡፡


በተለይ ትምህርቱ ተግባር የማያውቀው መሆኑ፤ ተማሪዎች ከተመረቁም በኋላ ቢሆን በስራ አለም ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል በሚል በብርቱ ይተቻል፡፡


ይህን የትምህርት ችግር ለመፍታት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ ያሉ፤ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና ባለሀብቶች አንድ ላይ ሆነው አንድ ተማሪ ቤት አቋቁመዋል፡፡


ስሙም ‘’አማና ሞዴል 2ኛ ደረጃ ት/ቤት’’ በሚል ሰይመውታል፡፡


የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ያለበትን ከፍተኛ የጥራት ችግር ለመፍታት፤ እንደ ስሜ አደራ ያለበት፣ ለሌሎች አርአያ የሚሆን ትምህርት ለመስጠት ነው የተቋቋምኩት ብሏል፡፡


አማና ሞዴል ትምህርት ቤት ከሚቀጥራቸው መምህራን 50 በመቶ የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ለማድረግ ማሰቡንም አስረድቷል፡፡


አማና ሞዴል ትምህርት ቤት ያቋቋሙት ባለሀብቶች ትምህርት ቤቱን ከማቋቋማቸው በፊት በየትምሀርት ቤቱ የትምህርትና ጥራት ሊያስጠብቁ የሚችሉ ስራዎች ሲሰሩ መቆታቸውን ያስታወሱት የትምህርት ቤቱ መስራች እና የቦርድ አባል ኤሊያስ ረዲ ‘’ትምህርት ቤቱን የከፈትነው ትርፉን ወደ ኪሳችን ልንወስድ አይደለም፤ በትምህረት ላይ የምንስራውን በጎ አድራጎት ስራን አስፍቶ ለመስራት እንጂ’’ ብለዋል፡፡


የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት አሚና መኑር(ዶ/ር) "ትምህርት ቤታችን ለተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ትኩረት መስጠቱ፣ በማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዓይነቶች ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ያለንን ቁርጠኝነት አይቀንሰውም’’ ብለው በትምህርት ቤቱ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ሲናገሩ ሰምተናል።


የትምህርት ቤቱ መሥራች አባላት ‘’አማና ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት’’ን ከመመስረታቸው በፊት’’አማና የወጣቶች ልማት ኔትወርክ’’ የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት አቋቁመው ለትምህርት ጥራት አስተዋጽዖ የማበርከት ዓላማ ያለው ፕሮጀክት ቀርፀው በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባም ውጪ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተፈጥሮ ሳይንስ መምህራን የሳይንስ ትምህርቶችን በተግባር አስደግፎ በማስተማር ላይ ያተኮረ ነፃ የሥልጠና መርኃ ግብር ያካሂዱ እንደነበር በምረቃ ዝግጅቱ ላይ ተነግሯል፡፡


በአዲስ አበባ ግሎባል ሆቴል ፊት ለፊት የተከፈተውን ት/ቤት የምረቃ ስነስርዓትን በክቡር እንግድነት የከፈቱት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ‘’ትምህርት ቤቱ በትምህርት ጥራት ላይ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ በስነ ምግባር እና ግብረ ገብ ላይ በርትቶ እንዲሰራም አደራ’’ ብለዋል፡፡


በ20 ሚሊዮን ብር የተመሰረተው ‘’አማና ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት’’ በተለይ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች በተግባር በማስደገፍ ከመጪው ዓመት የትምህርት ዘመን ጀምሮ ስራ እንደሚጀምር ሰምተናል፡፡


ንጋቱ ሙሉ


ความคิดเห็น


bottom of page