‘’በሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ አባላት ከስነ-ምግባር መመርያው ውጪ ኦፕሬሽን ሰርታቹሀል ተብለው በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተፈርዶባቸው በእስር ላይ ናቸው’’ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት አበባው ደሳለው የተባሉ የፓርላማ አባል፤ ‘’ባለፉት 10 ወራት በአማራ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ በማድረግ የመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል’’ የሚል ጥያቄ ባቀረቡላቸው ወቅት ነው፡፡
የፓርላማ አባሉ ‘’በክልሉ አንዳንድ ከተሞች የጅምላ ግድያ በፀጥታ ሀይሎች ተፈፅመዋል፣ ለማሳያም በመራዊ ፣ በደብረ ኤልያስ ፣ በፍኖተ ሰላም እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈፅሟል’’ ሲሉ አንስተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 36ኛ መደበኛ ስብሠባ ሲካሄድ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራርያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወታደራዊ ፍርድ ቤት በእስር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
“ለስህተቶቹ ሃላፊነት መውሰድ አለብን” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወታደራዊ ፍርድቤቶች ጥፋተኛ ተብለው በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
አባላቱ በአስር ላይ የሚገኙት ‘’በማይገባ መንገድ ኦፕሬሽን ሰርታቹሃል በሚል ምክንያት ነው’’ ብለዋል፡፡
‘’የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የጅምላ ግድያ ላይ ተሳትፈዋል’’ በሚል የሚቀርበው ወቀሳ ግን ‘’መሰረተ ቢስ’’ ያሉት
ዐቢይ አህመድ ‘’የኢትዮጵያ መንግስት እና ወታደር በጅምላ አይገድልም’’ ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments