ሰኔ 26 2017 - የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ጥራትን ከምፈትሽባቸው መለኪያዎች መካከል፤ ዕውቅና ያገኙት 48 ደርሰውልኛል አለ
- sheger1021fm
- 6 days ago
- 2 min read
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የአገልግሎት እና የምርት ጥራትን ከምፈትሽባቸው መለኪያዎች መካከል፤ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ዕውቅና ያገኙት 48 ደርሰውልኛል አለ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ እውቅናዎቹን አግኝቻለሁ ያለው፤ በምግብ አምራቾች እና ድህረ ገበያ ቅኝት፣ በመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች ላቦራቶሪ እና መሰል መለኪያዎች ነው፡፡
አለም አቀፉ የጥራት አረጋጋጭ ተቋም #ISO (International Organization for Standardization ) የሚያስቀምጣቸውን መስፈርቶች በሟሟላት፤ ከአሜሪካው ‘’አንሲ ናሽናል’’ አክሪዲቴሽን ቦርድ ጨምሮ፣ ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት በተለያዩ መለኪያዎች መ/ቤቱ ዕውቅና ማግኘቱ ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ፤ ባለስልጣኑ እነዚህን ዓለም አቀፍ እና ሀገር ዓቀፍ እውቅና ማግኘቱ፤ በአፍሪካ በዘርፉ ተጠቃሽ ተቋም ለመሆን ያስቀመጠው ዓላማ ለማሳካት ይረዳዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ለተለያዩ ተቋማት የጥራት እውቅና ለመስጠት በቅድሚያ እሱም ከዓለም አቀፉ የጥራት መለኪያ ማረጋገጫ ተቋም እውቅና ማግኘት እንዳለበት የተነገረ ሲሆን፤ አሁን ለኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን እውቅና የሰጠባቸው ዘርፎችም በዚሁ በዓለም አቀፍ መስፈሪያዎች ያለፍኩባቸው ናቸው ብሏል፡፡
የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አክሊሉ ጌታቸው፤ እነዚህ እውቅናዎች ተቋማት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚረዷቸው ናቸው ብለዋል፡፡
አንድን ምርት ወይም አገልግሎት በአለም አቀፍ ደረጃ አውቅና እንዲያገኝ ወደ አለም አቀፍ ተቋማት በሚሄበት ሂደት ብዙ ዶላር ወጪ እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት አለም ዓቀፍ መስፈርቶች አሟልቶ በተገኘባቸው መለኪያዎችም፤ ለሌሎች ተቋማት እውቅና መስጠት እንደሚችል የጠቀሱት ሀላፊው ምርትና አገልግሎቴ እውቅና ያግኝልኝ የሚሉ ድርጅቶች ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንደሚመዝኑም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ የውድድር ዓለም፤ በአለም አቀፍ ገበያ ተዓማኒነት ለማትረፍ እና ተወዳዳሪ ለመሆን አለም አቀፍ የምርት እና ጥራት መለኪያዎች ላይ እውቅና ማግኘት ያስፈልጋል ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ እጀምረዋለሁ በአለቸው የአፍሪካ ንግድ ቀጠናም፤ በሚገቡም ሆኑ በሚወጡ ምርቶች ግብይት ላይ እነዚህ የአለም አቀፍ መለኪያ መስፈርቶች ጥቅማቸው የበዛ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ የተገኙ የጥራት መስፈርቶች ጠቃሚ እንደሆኑ ያስረዱት የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባ(ዶ/ር)፤ በአገልግሎት ወቅት ቅልጥፍና እንደሚጎድል ጠቅሰው፤ ተቋማቱ ከጥራት ባሻገር ቅልጥፍናም ሊያዳብሩ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አለም ዓቀፍ እና ሀገር ዓቀፍ እውቅና ካገኘባቸው መለኪያዎች መካከል፤ የመድኃኒት ኢንስፔክሽን፣ ምግብ ጥራት ምርመራ ላቦራቶሪ፣ በህክምና ጓንት ጥራት ምርመራ፣ በመድኃኒትና ኮንዶም ጥራት ምርመራ ላቦራቶሪዎች ተጠቅሰዋል፡፡
የተሰጡ እውቅናዎች በጊዜ ገደብ የሚገመገሙ እና መስፈርቱን ካጎደሉ ደግሞ እውቅናውን የመነጠቅ እድልም መኖሩም ሰምተናል ፡፡
ለዚህም ባለስልጣኑ በቅርቡም ሆነ ቀድሞ የተሰጠው እውቅናዎች ለማስቀጠል እና ለላመነጠቅ በበርቱ መስራት ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments