በአጠቃላይ ግብር ከሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት ግጭት ውስጥ ያሉት ከፍተኛ ግብር የሚሰበሰብባቸው መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ተናግሯል፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ያለው ለአንድ ዓመት ሲካሄድ የቆየውን የታክስና ጉምሩክ ህግ ተገዥነት ንቅናቄ መጠናቀቁን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ነው፡፡
የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ በስም የጠቀሷቸው የጅማ፣ የባህር ዳርና የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ለወትሮው ከፍተኛ ገቢ የሚሰበሰብባቸው ቢሆኑም በዘንድሮ ዓመት ግን በእነዚህ ቅርንጫፎች ገቢ ለመሰብሰብ ተቸግረናል ብለዋል፡፡
ይሁንና ሚኒስትሯ ተቸግረናል ከማለት ውጪ ምን ያህል ለመሰብሰብ ታስቦ ምን ያህሉ ሳይሰበሰብ ቀረ የሚለውን ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡
እዚህም እዚያም ያለው ግጭት የንግድ እንቅስቃሴውን አውኮታል፤የገቢ አሰባሰቡ ላይም ቀጥተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡
ከክልሎች የሚበሰበው የገቢ ግብር በፌድሬሽን ምክር ቤት ቀመር መሰረት ግማሽ ያህሉ ተመልሶ ወደ ክልሎች የሚሄድ ነው የሚሉት ሚኒስትሯ የገቢው አለመሰብሰብ መልሶ ክልሎችን እንደሚጎዳም ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል አብዛኞቹ ግብር ከፋዮች ህግና ስርዓቱን ተከትለው ግብራቸውን የሚከፍሉ ቢሆንም፤ ባለፉት 11 ወራት ከግብር ማጭበርበር፣ ከህገወጥ ንግድና ከኮንትሮባንድ 106 ቢሊዮን ብር የተገመቱ ቁሳቁሶች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ተናግረዋል፡፡
በግብር ማጭበርበርና በኮንትሮባንድ ወንጀል የተጠረጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳያቸው በህግ ተይዞ ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ከመካከላቸም እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራት የተቀጡም እንደሚገኙበት ሲነገር ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments