top of page

ሰኔ 25 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Jul 2
  • 2 min read

በጋዛ ሰርጥ ለፍልስጤማውያን ሰብአዊ እርዳታ በማቅረብ ላይ የተሰማራው GHF እንዲዘጋ ተጠየቀ፡፡


ጥያቄውን ያቀረቡት ከ130 በላይ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


GHF የእርዳታ አቅርቦቱን በማወሳሰብ የፍልስጤማውያኑን እርዳታ ፈላጊዎች ችግር በማባባስ ስሙ በክፉ ይነሳል፡፡


ድርጅቱ የአሜሪካ እና የእስራኤል ድጋፍ እንዳለው ይነገራል፡፡


በእርዳታ ማከፋፈያ ማዕከሎቹ በተፈጠሩ መተፋፈጎች ባለፉት ጥቂት ወራት ከ500 የማያንሱ ፍልስጤማውያን እርዳታ ፈላጊዎች ተተኩሶቸው ተገድለዋል ተብሏል፡፡

የ GHF የእርዳታ አቅርቦት ሥርዓተ አልበኝነት በብርቱ ሲነቀፍ ቆይቷል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን በድርጅቱ ላይ የሚቀርበውን ችግር አይቀበሉትም ተብሏል፡፡


በሌላ መረጃ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ለ60 ቀናት የተኩስ አቁም በሚደረግባቸው ሁኔታዎች ላይ መስማማቷን የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ፡፡


ትራምፕ የተኩስ አቁሙ በሚደረግበት ወቅት የጋዛው ጦርነት ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ከአጋሮቻችን ጋር እንሰራለን ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጉዳዩን በዝርዝር አላፍታቱትም ተብሏል፡፡


ለተኩስ አቁም ሲማፀን የቆየው የፍልስጤማውያኑ ታጣቂ ቡድን አዲስ ቀርቧል የተባለውን የተኩስ አቁም ሀሳብ ስለመቀበሉ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡


በሌላ መረጃ የየመን ሁቲዎች ትናንት ወደ እስራኤል ለተተኮሱት ሚሳየሎች ሀላፊዎቹ እኛ ነን ማለታቸውን ሐርቴዝ ጽፏል፡፡


ሁቲዎቹ የተኮስናቸው ሚሳየሎች በኤርፖርቶች እና በወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ያነጣጠረ ናቸው ብለዋል፡፡


የእስራኤል የጦር ሹሞች ሁቲዎቹ የተኮሷቸውን ሚሳየሎች መትተው እንዳጨናገፏቸው ተናግረዋል፡፡


ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ የየመንን አብዛኛውን የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን የጦር እና የፖለቲካ አጋሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡



የኮንጎ ኪንሻሣ ጦር የአገራችንን የአየር ክልል ጥሶ ገብቷል ያለውን አውሮፕላን መትቶ መጣሉን እወቁልኝ አለ፡፡


አገሪቱ ሰላም በራቀው የአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ተመትቶ መውደቁን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


አውሮፕላኑ ተመትቶ የወደቀው አገሪቱ ከሩዋንዳ በምትዋሰንበት የድንበር አካባቢ መሆኑ ታውቋል፡፡


የኮንጎ ወንዝ ህብረት የተሰኘው የአማጺያን ጥምረት አውሮፕላኑ ሰብአዊ እርዳታ ጭኖ በመምጣት ላይ የነበረ ነው በሚል ተቃውሞ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡


የኮንጎ ኪንሻሣ የጦር ሹሞች ግን ተመትቶ የወደቀው አውሮፕላን ወደ አየር ክልላችን ለመግባት ፈቃድ አልነበረውም ብለዋል፡፡

የኮንጎ ወንዝ ሕብረት የተሰኘው የአማፂያን ጥምረት አውሮፕላኑ ሰብአዊ እርዳታ በማጓጓዝ ላይ ነበረ ቢልም ይሄን ጉዳይ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ እንዳልተቻለ ተጠቅሷል፡፡


በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ሰፊ አካባቢን በጦር ተቆጣጥሮ የሚገኘውን የM 23 አማጺ ቡድንም አንዱ የጥምረቱ አካል እንደሆነ መረጃው አስታውሷል፡፡


የጋና ፖሊስ በታላላቅ የውጭ አገር የእግር ኳስ ቡድኖች እናስቀጥራችኋለን በሚል ማጭበርበር ወደ ናይጀሪያ ተወስደው የታገቱ 76 የአገሪቱን ወጣቶች አስለቀቅኳቸው አለ፡፡


በውጭው አለም ታዋቂ የእግር ኳስ ቡድኖች እናስቀጥራችኋለን በሚል ማጭበርበሪያ ወደ ናይጀሪያ የተወሰዱት ጋናውያን ወጣቶች ተንቀሳቃሽ ስልካቸው እየተቀማ በአንድ ቤት ውስጥ ተፋፍገው መገኘታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ለስልጠና ወጪ መሸፈኛ በሚል ሰበብ ወላጆቻቸው በነፍስ ወከፍ 1 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንዲልኩላቸው እንዲያደርጉ ሲገደዱ ነበር ተብሏል፡፡


ናይጀሪያ ውስጥ የዚህ ወንጀል አቀናባሪዎች ናቸው የተባሉ 7 ጋናውያን መያዛቸው ታውቋል፡፡


የጋና ፖሊስ ታጋች ዜጎቹን ነፃ ያወጣቸው በናይጀሪያ ፖሊስ ትብብር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


አለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት /ኢንተርፖልም/ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን መረጃው አስታውሷል፡፡



አሜሪካ በሶሪያ ሐያት ታህሪር አል ሻም የተሰኘውን የቀድሞ የአማጺያን ጥምረት ከአሸባሪነት መዝገቧ ልትፍቀው ነው፡፡


በምህፃሩ HTS የተሰኘው ጥምረት በቀደመው ጊዜ በአሜሪካ መንግስት በአሸባሪነት የተፈረጀ እንደነበር ሚድል ኢስት ሞኒተር አስታውሷል፡፡


HTS ከመንፈቅ በፊት በትጥቅ አመፅ የቀድሞውን ፕሬዘዳንት ባሻር አል አሳድን አስተዳደር ማስወገዱ ይታወቃል፡፡


አህመድ አልሻራ የጥምረቱ የበላይ ሲሆኑ ሶሪያንም በጊዜያዊ ርዕሰ ብሔርነት እየመሩ ነው፡፡


የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርብ ጊዜው የሳውዲ አረቢያ ጉብኝታቸው በተጓዳኝ አልሻራን አነጋግረዋቸዋል፡፡


ሰሞኑን ትራምፕ በሶሪያ ላይ ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ እንዲነሳ የሚያስችል ትዕዛዝ ፈርመዋል፡፡


አሁን ደግሞ ሶሪያን በበላይነት የሚያስተዳድረውን HTSን ከአሸባሪዎች ዝርዝር ሊፍቁት ነው ተብሏል፡፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…





Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page