የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት ከፍ እያለ ቢመጣም የጥራቱ ጉዳይ ግን አሳሳቢ መሆኑን አጥኚዎች ስጋታቸውን ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
በአዲስ ዩንቨርስቲ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር በላይ ሀጎስ የኢትዮጵያ የድህረ ምረቃ ትምህርት ችግር ሲጠቅሱ በቂ መምህራን አለመኖርን ያነሳሉ፡፡
አንዳንድ የድህረ ምረቃ ትምህርት ክፍሎች ከነጭራሹኑ ማስተማር የሚችል መምህር የሌላቸው አሉ ብለዋል፡፡
ለድህረ ምረቃ መግቢያ የሚሰጠው ፈተና ከባድ ከሚባሉ ፈተናዎች ውስጥ የሚመደብ መሆኑን በጥናታቸው ያሳዩት ዶክተር በላይ ውጤቱ ተማሪው አልፎ ትምህርት ቢጀምር ምን አይነት አቅም እንዳለው ማመልከት የሚችል ነው ይላሉ፡፡
በጥናታቸው ውስጥ በ2009 ትምህርት ሚንስቴር 11 አዳዲስ ዩንቨርስቲዎችን ለመክፈት በቂ መምህራን ለማግኘት በሚል ከሁሉም ዩንቨርስቲዎች በወቅቱ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ 10ሺ ተመራቂ ተማሪዎች ለእጩ መምህራን ተመልምለው ፈተና ቢወስዱም ማለፍ የቻሉት 716 ብቻ ነበር፡፡
እነዚህ ችግሮች ለመፍታት ጥራት ያለው ትምህርት እንደ ሀገር ለማምጣት ከተፈለገ ቅድሚያ ብቁ መምህራን መፍጠሩ ላይ ሊሰራ ይገባል የሚል ምክር አላቸው ተመራማሪው ዶክተር በላይ ፡፡
በተለይም የድህረ ምረቃ ትምህርት ክፍሎች ከወዲሁ ሊፈተሹ ይገባል ፣ደረጃቸው በምን ሁኔታ ይገኛል የሚሉ ጉዳዮች ከወዲሁ ሊታይ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚከፈቱት የትምህርት ክፍሎች አብዛናዎቹ ተመሳሳይ ናቸው የሚሉት ዶክተር በላይ መደረግ ያለበት ግን ተቋማቱ የራሳቸው ጥናትና ምርምር በማድረግ የተሻለ ካሪኩለም በመቅረጽ እራሳቸው የሚመስል የትምህርት ክፍል መክፈት ነው ሲሉ ያስረዳሉ ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ 49,000 የዩኒቨርሲቲ መምህራን ያሉ ሲሆን 4.4 ከመቶ የሚሆኑት ፕሬፌሰር ፣6 ከመቶ የሚሆኑት እረዳት ፕሮፌሰሮች ናቸው፡፡
ከ24 ዓመት በፊትለመጀመሪያ ጊዜ የድህረ ምረቃ ትምህርት ሲጀመር የነበረው የማስተስር ዲግሪ ተማሪዎች 959፣ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ 10 ብቻ ነበሩ፡፡
ይህ አሀዝ አሁን ላይ ከፍ ብሎ የማስተርስ ዲግሪ ተማሪዎች 68,000፤ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎች ደግሞ 5,000 ደርሷል፡፡
የጥናቱ መረጃው ሙሉ ለሙሉ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ላይ መሰረት ያደረገ ነው፡
በረከት አካሉ
Comments