ሰኔ 23 2017 - ክልሎች ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር በሚል፤ ህግ ወጥ ኬላዎችን እንደሚያቋቁሙ በጥናት መረጋገጡን ተ ነገረ
- sheger1021fm
- Jun 30
- 2 min read
ክልሎች ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር በሚል፤ ህግ ወጥ ኬላዎችን እንደሚያቋቁሙ የጉምሩክ ኮሚሽን በጥናት መረጋገጡን ተናገረ፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ይህን የተናገረው የ11 ወር የስራ ክንውን ሪፖርቱን ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡
ባለፉት 11 ወራት 19 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የተናገረው የጉምሩክ ኮሚሽን፤ በየክልሎች ገመድ እየተወጠረ ገቢ የሚሰበስብባቸው ህገ ወጥ ኬላዎች በሀገሪቱ ንግድ ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ህገ ወጥ ኬላዎች በነፃ የንግድ ዝውውር ላይ ጫና እያሳደሩ በመሆኑ፤ ይህ ችግር በቀጣይ በጀት ዓመትም እንዳይቀጥል ምን እየተሰራ ነው? ሲል ጠይቋል፡፡
ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ አዘዘው ጫኔ ኬላዎቹ ህገ ወጦች ቢሆኑም ገመድ ወጥረው የሚሰበስቡት ገቢ ግን የመንግስት ተቋማት ናቸው ብለዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሰጪነት ከንግድ እና ቀጠናዊ ሚኒስቴር እና ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲከስ ሚኒስቴር ጋር በመሆን በሚያዚያ ወር በተጠናቀቀ ጥናት 237 ህገ ወጥ ኬላዎች መኖራቸውን ተረጋገግጧል ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ፡፡
ኬላዎችን ዘርግተው ግብር የሚሰበስቡት የክልለ ፖሊሶች፣ የሚሊሻ መዋቅሮች እንዳንድ ቦታ ደግሞ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እና በወረዳ ግብረ ሃይል ተብሎም ጭምር የተቋቋሙ ኬላዎች እንዳሉ ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ አዘዘው ጫኔ ተናግረዋል፡፡
ይህም በአብዛኘው የሀገር አቋራጭንም ጨምሮ የሀገር ውስጥ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መሳደሩን ምክትል ኮሚሽነሩ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡
በተደጋጋሚ ህገውጥ ኬላዎች እንዲነሱ ከተለያዩ አካላት ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ለማሳያ ባለፈው ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ያቀረበው የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ሕገወጥ ኬላዎች በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ እንቅፋት መሆናቸውን ተናግሮ፤ ባደረግነው ክትትል በዚህ ተግባር ውስጥ የክልል፣ ወረዳና የከተማ መስተዳድሮች በድብቅ እንደሚሳተፉ አረጋግጠናል ማለቱ ይታወሳል፡፡
ከሳምንት በፊት በተመሳሳይ ሪፖርቱ ለምክር ቤት አቅርቦ የነበረው የንግድ እና ቀጠናዊ ሚኒስቴርም መሰል ጥያቄ ተነስቶለት በህገ-ወጥ ኬላዎች ገቢ የሚሰበስቡ አካላት መኖራቸውን አረጋግጦ ኬላው እንዲነሳ እየተሰራ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ይሁንና ኬላዎቹ እንዲነሱ እየጮሁ ያሉት መሳሪያ የሚያስገቡ አካላትም መሆናቸውም መታወቅ አለበት ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር፡፡
በህጉ መሰረት ኬላዎችን ማቋቋም የጉምሩክ ስልጣን ነው ያሉት አቶ አዘዘው ህግ ወጥ ኬላዎችን ግን ክልሎች ያቋቋሙበት ሁኔታ መኖሩ ጠቅሰዋል፡፡
ችግሩ 2018 በጀት ዓመት ይቀረፋል የሚል እምነት አለንም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የገቢዎች ሚኒስቴር በ2017 በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ታክስ እና ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ ብር 900.27 ቢሊየን ለመሰብሰብ አቅጄ በ11 ወራት 815.3 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ችያለው ብሏል፡፡
ይህም ከእቅዱ አንፃር 100 በመቶ የተሳካ ሲሆን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር የ349.3 ቢሊየን ብልጫ አለው ብሏል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments