top of page

ሰኔ 22፣ 2016 - ''ቦርዱ፤ ፓርቲዎች በሚያቀርቡት የሴትና የአካል ጉዳተኛ አባላት ብዛት ልክ የገንዘብ ድጎማ ይሰጣል'' ምርጫ ቦርድ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ገዢው ፓርቲን ጨምሮ የተጋነነ የሴቶችና አካል ጉዳተኛ አባላትን ቁጥር ያቀረቡ ፓርቲዎችን አስጠነቀቀ፡፡


የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በዘንድሮ ዓመት ገዢውን የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ዓመት ውስጥ ከ10,000 እስከ 900,000 የሴት የሴትና አካል ጉዳተኛ አባላት ቁጥር አቅርበዋል አለ፡፡


ለፓርቲዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጎማ ፓርቲዎቹ በሚያቀርቡት የሴትና አካል ጉዳተኞች ቁጥር የሚወስነው ቦርዱ፤ የሁሉንም መረጃ የመረመረ ሲሆን ከመካከላቸው የ11ዱ ፓርቲዎች ቁጥር የተጋነነ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡


ቦርዱ ፓርቲዎቹ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የሁሉንም አባላቱን ዝርዝር ካላቀረቡ ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ብሏል፡፡


የብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሰኔ 20 ጀምሮ ለተከታታይ 7 ቀናት የአባሎቻቸውን ሙሉ መረጃ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ አሳስቧል፡፡


ቦርዱ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ፓርቲዎች በሚያቀርቡት የሴትና የአካል ጉዳተኛ አባላት ብዛት ልክ የገንዘብ ድጎማ ይሰጣል፡፡

አንድ ፓርቲ ከአጠቃላይ አባላቱ ምን ያህሉ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ናቸው የሚለውን እያየ ገንዘቡን ይሰጣል ማለት ነው፡፡


ፓርቲዎቹ ከቦርዱ የሚያገኙት የገንዘብ መጠን በሚቀርቡት ሴትና አካል ጉዳተኛ አባላቱ መጠን እንደሚወሰን በአዋጁ ተቀምጧል ይላሉ በቦርዱ የስርአተ ፆታ ባለሞያ ዮርዳኖስ ተወልደ ነግረውናል፡፡


ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደሚነሳው ፓርቲዎች እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች እምብዛም ትኩረት አይሰጧቸውም፡፡


በ6ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተሳተፉ በፓርቲ የታቀፉ ሴቶች ከ1,900 ያልበለጡ ናቸው የአካል ጉዳተኞች ቁጥርም ከዚህ ያነሰ ነው ይላሉ ባለሙያዋ፡፡


ይሁንና በዘንድሮ ዓመት ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች እጅግ የተጋነነ የሴትና አካል ጉዳተኛ አባላት ቁጥር ለቦርዱ አቅርበዋል ተብሏል፡፡


ገዢው የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች በ2016 ዓ.ም ለቦርዱ ያሳወቁት የሴት እና የአካል ጉዳተኞች አባላት በ2014 እና በ2015 ዓ.ም ካቀረቡት ቁጥር አንፃር የተጋነነ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል ቦርዱ፡፡


ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 21 ፖለቲካ ፓርቲዎች የአባሎቻቸውን ሙሉ መረጃ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም መረጃዎቹን እንዲያሳውቁ መጠየቁን ቦርዱ አስታውሷል፡፡


ይሁንና ከእነዚህ 21 ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ምላሾችን የሰጡ እና በእጃቸው የሚገኙ መረጃዎችን ያቀረቡት 10ሩ ብቻ ናቸው፡፡


11ዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ዓመት ውስጥ ከ10,000 እስከ 900,000 የሴት እና አካል ጉዳተኛ አባላት ቁጥር አቅርበዋል፡፡


ይሁን እንጂ ለዚህ አሐዝ ተገቢውን መረጃ እንዲቀርቡ ቢጠየቁም እስከ ሰኔ 20 ቀን 2016ዓ.ም ድረስ ምላሽ እንዳልሰጡ ቦርዱ ተናግሯል፡፡


ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫው ብልፅግናን ጨምሮ 11ዱም ፓርቲዎች ከሰኔ 20 ጀምሮ ለተከታታይ 7 ቀናት የአባሎቻቸውን ሙሉ መረጃ ለቦርዱ እንዲያቀርቡ በድጋሚ አሳስቧል፡፡

በእነዚህ በተሰጡት ቀናት መረጃዎቹን የማያቀር ከሆነ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አስጠንቅቋል፡፡


ህጋዊ የተባለው እርምጃ ምንድነው ስንል ቦርዱን ጠይቀናል፡፡


መረጃውን በማያቀርቡ ፓርቲዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ገና አልተወሰነም፤ ቀነ ገደቡ ሲጠናቀቅ ቦርዱ ተነጋግሮ የሚወስነውን ያሳውቃል የሚል ምላሽም አግኝተናል፡፡


የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንቱ ዐብይ አህመድን ጨምሮ ምክትላቸው አደም ፋራህ በተለያየ ጊዜያት እንደተናገሩት የአባላቱ ቁጥር 14 ሚሊዮን ደርሷል፡፡


ምርጫ ቦርድን አላሳመነኝም ያለው ከ14 ሚሊዮኑ ምን ያህሉ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ አልተለየም፡፡


ከብልፅግና በተጨማሪ ቦርዱ ያቀረባችሁት የሴቶችና አካል ጉዳተኞች ቁጥር አላሳመነኝም ያላቸው ፓርቲዎች፡-


  • የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት

  • የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ

  • የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን

  • የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር

  • የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ

  • የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ

  • የጋምቤላ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ

  • አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት

  • ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲና

  • የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ናቸው፡፡


ምንታምር ፀጋው


Коментарі


bottom of page