ሰኔ 21፣ 2016 - በድንበር አካባቢዎች የሚገኙና በተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች እየተተገበሩ ላሉና ለታቀዱ ፕሮጀክቶች የሚሆን ውል መታሰሩ ተነገረ
- sheger1021fm
- Jun 28, 2024
- 2 min read
በኢትዮጵያ በድንበር አካባቢዎች የሚገኙና በተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች እየተተገበሩ ላሉና ለታቀዱ ፕሮጀክቶች ለግንባታና ለማማከር የሚሆን ውል መታሰሩ ተነገረ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች እየተተገበሩ ላሉና ለታቀዱ ፕሮጀክቶች በ412,000,000 ብር ወጪ የግንባታና የማማከር ውል ስምምነት መፈራረሙ ተነግሯል።
የውል ስምምነቱን የፈረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ናቸው፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሀ ፕሮጀክት በአለም ባንክ ገንዘብ ድጋፍ በ55 ወረዳዎች 110 ቀበሌዎች በድንበር አካባቢዎች በተደጋጋሚ ድርቅ በሚከሰትባቸው እና ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች እየተተገበሩ ላሉና በዕቅድ ለተያዙት ፕሮጀክቶች በግንባታና በማማከር ስራ ውል መገባቱን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዲኤታው የተፈረመው የውል ስምምነት 371,000,000 ብር የመካከለኛ መጠጥ ውሃ ግንባታ ከአራት ኮንትራክተሮች ጋር እንዲሁም ቀሪውን 41,000,000 ብር ደግሞ ከ5 አማካሪ ድርጅቶች ጋር ለ6 ሳይቶች የማማከር ስራ የሚከወንበት ነው ብለዋል፡፡

ድርጅቶቹ ስራውን በተያዘላቸው የጌዜ ገደብ በፍጥነትና በጥራት ሰርተው የህብረተሰቡን ችግር በመፍታት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ስምምነቱ የ6 ወር የጊዜ ቆይታ ሲኖረው በሶማሌ፣ በአማራና እና በሌሎች ክልሎች በሚገኙ 9 ወረዳዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰምተናል፡፡
በሌላ በኩል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ515,000,000 ብር በላይ በሚሆን ወጭ የቅድመ ጎርፍ መከላከል የሲቪል ስራዎችን ለማከናወን ከአምስት ተቋራጭ ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱን የተፈራረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ(ዶ/ር) የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራው የአጭር ጊዜ መፍትሄ ለመስጠት የሚሰራ በመሆኑ ከሚገኘው ትርፍ በላይ ሰዎችን ከአደጋ የሚታደግ በመሆኑ በተቀመጠው አጭር ጊዜ ስራውን በመከወን ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በተለይም አፋር ላይ ችግሩ የከፋ በመሆኑ የጎርፍ አደጋውን መከላከል ብቻ ሳይሆን የውሃ ስርጭቱንም ለመቆጣጠር የሚያግዝ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ሚኒስትር ዲኤታው፡፡
ስምምነቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል በላይኛው አዋሽ 7 ወረዳዎች ላይ የጎርፍ ቅድመ መከላከል ስራ፣ በአፋር ክልል ደግሞ በመካከለኛው አዋሽ ለሚከናወነው የቅድመ ጎርፍ መከላከል፣ በታችኛው አዋሽ የቅድመ ጎርፍ መከላከል የግንባታ ስራዎች ለመከወን ከ 5 የግንባታና የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ተቋራጮች ጋር ተፈራርሟል፡፡
ስራው በሁለት ወር ጊዜ ተሰርቶ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
ምህረት ስዩም
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Commentaires