በኢትዮጵያ ባሉት አራት ወቅቶች መሰረት የክረምት ወራት ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያሉት 3 ወራትን የሚሸፍን ቢሆንም የዘንድሮ ክረምት ከጊዜው ቀድሞ ገብቷል፡፡
ክረምቱን ተከትሎ የአየር ጠባዩ በመቀየሩ አለባበስንም ለመቀየር ያስገድዳል፡፡
ወፈር ያሉ፣ ሙቀትን የሚሰጡ፣ ቀለማቸውም በአብዛኛው ፈዘዝ ያሉ አልባሳትና ጫማዎች በዚህ ወቅት ይዘወተራሉ፡፡
እኛም በዛሬው የገበያ ውሏችን ለክረምቱ የሚሆኑ አልባሳትና ጫማዎች ግብይት እንዴት እየተከናወነ ነው ስንል ገበያውን ዞር ዞር ብለን ቃኝተናል፡፡
የክረምቱን ብርድና ጭቃ መቋቋም የሚችሉ ቡትስ ጫማዎች በሀገር ውስጥ የሚሰሩት ከ1,000 ብር ጀምሮ እስከ 2,500 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
ከውጭ ሀገር የሚገቡት እፈልጋለሁ ለሚል ሸማችም ከ2,500 ብር እስከ 10,000 ብር የሚሸጥ ቡትስ ጫማ ተመልክተናል፡፡
የጫማዎቹ ዋጋ እንደ መጡበት ሃገር፣ እንደሚሰጡት ምቾት፣ እንደ ጥንካሬያቸው ይለያያል፡፡
ረጅም ሆነው የተሻለ ምቾት አላቸው የሚባሉት ከ 8 እስከ 10 ሺህ ብር እንደሚሸጡ ከነጋዴዎቹ ሰምተናል፡፡
ከጫማዎች በተጨማሪ ብርዱን ለመቋቋም የሚረዱ አልባሳትም በዚህ ጊዜ ይፈለጋሉ፡፡
ጃኬቶች አይነታቸው የሚለያይ ሆኖ ለሴቶች የሚሆኑ ከ3,000 ብር ጀምሮ፣ ለወንዶች የሚሆን ጃኬት ከ4,000 ብር ጀምሮ ይገኛል፡፡
ጋውን እስከ 2,500 ብር ሹራብ የሴትም የወንድም ከ2,000 ብር ጀምሮ እየተሸጠ ነው፡፡
በግብይት ላይ እያሉ ያገኘናቸው ሸማቾች፤ የአልባሳቱም የጫማዎቹም ዋጋ በጣም ተወዷል፤ ከአቅማችን በላይ ሆኗል ብለውናል፡፡
ነጋዴዎቹ ግን የአልባሳትና ጫማዎች ዋጋ የእዳንዶቹ ከአምናው አንፃር ዋጋው ተቀራራቢ ነው፣ ብዙም ጭማሪ አላሳየም ባይ ናቸው፡፡
በሚቲዎሮሎጂ መስሪያ ቤቱ መረጃ መሰረት ክረምቱ እየጠነከረ፣ ዝናቡም እየከበደ መምጣቱ አይቀርምና ዣንጥላዎችም ተፈላጊ ናቸው፡፡
አነስ ያሉ በአባዛኛው ሴቶች የሚያዘወትሯቸው ዣንጥላዎች ከ550 ብር ጀምሮ እየተሸጡ ነው፡፡
ለወንዶች የሚሆኑት ተለቅ ያሉ ዣንጥላዎች ደግሞ ከ800 -1000 ብር ይሸጣሉ፡፡
በሌላ በኩል ለሴቶች የሚሆኑ ታይቶች ከ1,000 ብር እስከ 2,500 ብር ዋጋቸው ነው፡፡
ምንታምር ፀጋው
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Commenti