አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ጥራት እንዲልቅ፣ ሀኪሞች በተሻለ አቅም እንዲያገለግሉ እነዲሁም ለምርምርና ለተሻለ አገልግሎት ያግዘዋል የተባለ የ’’ስማርት ካምፓስ’’ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀመረለት።
የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በሂደት ላይ ላለው ለአዲስ አበባ ዩኒቨረሲቲ የተጀመረለት ይህ ፕሮጀክት ሲሳካ በዲጅታል መንገድ ብዙ የተንዛዙ አሰራሮችና አስተዳደራዊ ችግሮች ይፈታል መባሉን ሰምተናል።
በዓመት አንድ ሚሊየን ህዝብ ያስተናግዳል የተባለው የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከህክምና ጋር በተገናኘ የሚያስተናግደው ክፍያው በዲጅታል እንዲቀላጠፍም ሥርዓት ተዘርግቶለታል ተብሏል።
በዩኒቨርስቲው ስር በሚተዳደረው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያለው አሰልቺና አስተዳደራዊ ችግር በተለይ ከክፍያ ጋር ያለውን ችግር የተጀመረው የስማርት ካምፓስ ፕሮጀክት ያቀልልለታል መባሉን ሰምተናል።
ለስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ስማርት ካምፓስ መፍትሄ ለማቀበል ኢትዮ ቴሌኮም በአጋርነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተስማምቷል።
የጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይድ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ክፍያዎችም በቴሌብር ለመፈጸም የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ኩባንያው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስማርት መማሪያ ክፍሎችና የተለያዩ ዘመናዊ የዲጅታል አሰራሮችን ለመከወን ያስችላል ተብሏል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የትምህርት ጥራት የተሻለ እንዲሆንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለት እንዲሆን ያግዛል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) የሚገነባው ስማርት ካምፓስ ፕሮጀክት ለዩንቨርስቲው ጥልቅ ምርምርና የተሻለ ህክምና እንዲሰጥ ያግዘዋል ብለዋል።
የትምህርት መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት፣ የቤተ ሙከራ ፍተሻዎችን በተሻለ ተሞክሮ ለማከናወን፣ የምዘና ፈተናዎችን ለመስጠት፣ ለማረም እና ውጤቶችን ወዲያውኑ ለማሳወቅ የሚያስችል ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን (SMART CLASS ROOM) ለመገንባት ያስችላል ተብሏል።
ከዚህም ባለፈ የስድስት ኪሎ ካምፓስ ግቢ የመግቢያ በሮች፣ ዋና ዋና የአስተዳደር ህንጻዎችን፣ ሙዚየም፣ ካፊቴሪያዎች፣ የቤተ መጽሐፍት፣ የተማሪዎች እና የውጪ ሀገር ዜጎች የመኖሪያ ህንጻ ሰላማዊ እንቅስቃሴና ደህንነት ለመከታተል ፕሮጀክቱ እንደሚያግዝ ሰምተናል፡፡
ይህንንም ለማረጋገጥ ፕሮጀክቱ የሲሲቲቪ ካሜራ፣ የመቆጣጠሪያ ማዕከል እና የካምፓስ ፋይበር ኔትወርክ ዝርጋታ እንዲሁም ተዛማጅ የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚያካትት ነው ተብሏል።
በባዮሜትሪክስ፣ ኪውአር ኮድ ወይም አክሰስ ካርድ የሚሰሩ የተሽከርካሪ/ፓርኪንግ እና የባለጉዳይ አክሰስ ማኔጅመንት ዲጂታል ሶሉሽኖችን ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።
ይህም ፕሮጀክት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ሁሉን አቀፍ የስማርት ካምፓስ ፕሮጀክት ነው መባሉንም ሰምተናል።
ይህ ሲጠናቀቅም ዩኒቨርሲቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን ይችላል ተብሏል።
ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ካምፓሶች ጋር እንዲገናኝ የኔትወርክ የሚያስተሳስር ፕሮጀክት ተከናውኖለታልም ተብሏል።
ተህቦ ንጉሴ
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Comments