top of page

ሰኔ 20፣ 2016 - በተደረጉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች አርበኛ ማነው? የሚለው ግልፅ መሆን አለበት ሲል የምክክር ኮሚሽን ተናገረ

የውጭ ወራሪዎችን በመመከት ስማቸው የሚነሳ በርካታ አርበኞች ቢኖሩም የመንግስት ለውጥ ለማድረግም ሆነ ለሌላ አላማ በተደረጉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች አርበኛ ማነው? የሚለው ግልፅ መሆን አለበት ሲል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተናገረ፡፡


የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በሀገሪቱ በ4ቱም አቅጣጫዎች በተደረጉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች አርበኝነት የተሰጠው ለአንዱ ሊሆን ይችላል ለሌላው ደግሞ የተሸናፊነት አሊያም የበዳይነት ሊሆን ስለሚችል ይህን በአግባቡ መለየት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡


ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት ትናንት የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር እና የሰላም ሚኒስቴር ባሰናዱት መድረክ ላይ ነው፡፡


በመድረኩ ላይ አርበኝነት ለአንድነትና መፃሂ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የሚል ጥናታዊ ፅሁፉ ያቀረቡት የታሪክ መምህሩ ማህመድ ሐሰን( ዶ/ር) በእርስ በእርስ ግጭቶች ጀግና አለ ማለት አይቻልም ብለዋል፡፡


ጀግና ማለት ሀገርን ከጥፋት፣ ከመበታተን እና ከወራሪ የሚጠብቅ ነው እንጂ አንድን ሥርዓት ለመጣልም ሆነ ለሌላ ጉዳይ በተደረገ ጦርነት የተሳተፈ አይደለም ብለዋል፡፡

ብሔራዊ ጀግና፣ ሰንደቅ ዓላማ፣ ህገ መንግስትና ሌሎቹም ጉዳዮች እኩል ያላግባቡና እያጨቃጨቁ ያሉ ጉዳዮች መሆናቸው በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡


በሀገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል ተብሎ በታሰበው ምክክርም እነዚህ አጀንዳዎች አዲስ አበባን ወክለው ከቀረቡት ውስጥ መሆናቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡


ያሬድ እንዳሻው

Comments


bottom of page